ቀጥታ፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከተሞችን የኢኮኖሚ ማዕከል በማድረግ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቷል

አሶሳ፤ ጥቅምት 6/2019 (ኢዜአ)፦ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከተሞችን የኢኮኖሚ ማዕከል በማድረግ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ ከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ ኢሳቅ አብዱልቃድር ገለጹ።

የመደመር መንግሥት ከተሞችን ሁለንተናዊ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ እንቅስቃሴ ማዕከል በማድረግ የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የአጭርና የረጅም ጊዜ ዕቅዶችን በመቅረጽ ወደ ሙሉ ትግበራ ገብቷል። 

በዚህም መሠረት የከተሞችን ገጽታ የሚያድሱና የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎችን የሚያፋጥኑ የኮሪደር ልማት ሥራዎች፣ የሥራ ዕድል ፈጠራዎች እንዲሁም የአገልግሎት አሰጣጥን የሚያዘምኑ የአንድ ማዕከል አሠራሮች ሕብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ በስፋት እየተከናወኑ ይገኛሉ።


 

በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢሳቅ አብዱልቃድር እንደተናገሩት፤ በመደመር መንግስት የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተከናወኑ ተግባራት ውጤት እያመጡ ናቸው።

በተለይም ከተሞችን የኢኮኖሚ ማዕከል በማድረግ ለሥራ እድል ፈጠራና ገጽታ ግንባታ ወደ ሥራ መገባቱን ገልጸዋል።

የከተማ ልማት ሥራዎች፣ የኮሪደር ልማት፣ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ማዕከላትንና መሠረተ ልማቶችን ሕብረተሰቡን በማስተባበር በመስራት በተያዘላቸው ፍጥነትና ጥራት ለማከናወን መታቀዱንም አስረድተዋል።


 

የመደመር መንግስት ለህዝቡ የገባውን ቃል በተግባር በማዋል ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግም ትኩረት መስጠቱን ጠቁመዋል።

ከከተሞች የኮሪደር ልማት እና የመሠረተ ልማት ሥራዎች በተጨማሪ የገጠር ኮሪደር ልማት ሥራዎች የህብረተሰቡን ተሳትፎ በማጠናከር ይከናወናል ብለዋል።

ከተሞችን በመሠረተ ልማት ከማዘመን ጎን ለጎን በነዋሪዎች የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን የማስፋፋት ሥራ እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም