ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ እና ዩናይትድ ኪንግደም ስትራቴጂካዊ አጋርነታቸውን እንደሚያጠናክሩ ገለጹ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 6/2019 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና ዩናይትድ ኪንግደም በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተውን ስትራቴጂካዊ አጋርነታቸውን የበለጠ ለማጎልበት ቁርጠኛ መሆናቸውን አስታወቁ። 

በታይላንድ ባንኮክ እየተካሄደ የሚገኘው የ2026 የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና የዓለም ባንክ ዓመታዊ ስብሰባ ዛሬ አምስተኛ ቀኑን ይዟል።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) የተመራ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በስብሰባው ላይ እየተሳተፈ ነው።


 

የኢትዮጵያ ልዑክ ከስብሰባው ጎን ለጎን ከዩናይትድ ኪንግደም ዓለም አቀፍ ልማትና የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር ክርስቲ ማክኔል ጋር ውይይት አድርጓል።

ውይይቱ በወቅታዊ የኢኮኖሚ ሁኔታዎች እና ኢትዮጵያ ዘላቂ የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትና የረጅም ጊዜ እድገትን ለማረጋገጥ የቅድሚያ ትኩረት በሰጠቻቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው።

በተጨማሪም ውይይቱ አሁን ባሉ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ሁነቶች ላይ ሀሳብ ለመለዋወጥ ምቹ አጋጣሚን ፈጥሯል።

ሚኒስትር ክርስቲ ማክኔል ኢትዮጵያ በመርህ ላይ ተመስርታ እያከናወነች ያለችውን ጥረት አድንቀዋል።

ሀገሪቱ ለቀጣናዊ ሰላም፣ መረጋጋት እና ልማት እያበረከተች ያለውን ስትራቴጂካዊ አስተዋጽኦ አንስተዋል።  

ዩናይትድ ኪንግደም ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ሁለንተናዊ የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ያላትን ጽኑ አቋም አረጋግጠዋል።

ሁለቱም ወገኖች ገንቢ ውይይቶቻቸውን አጠናክረው ለመቀጠል እና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተውን ስትራቴጂካዊ አጋርነታቸውን ይበልጥ ለማጎልበት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም