የሃይማኖት ተቋማት ለአብሮነት እና ለብሔራዊ መግባባት ያላቸውን ከፍተኛ ሚና ማጠናከር አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
የሃይማኖት ተቋማት ለአብሮነት እና ለብሔራዊ መግባባት ያላቸውን ከፍተኛ ሚና ማጠናከር አለባቸው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 6/2019 (ኢዜአ)፦ የሃይማኖት ተቋማት ለአብሮነት፣ ለአንድነት እና ለብሔራዊ መግባባት ያላቸውን ከፍተኛ ሚና ማጠናከር እንዳለባቸው የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ረታ ገለጹ።
የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ከሃይማኖት ተቋማት መሪዎች ጋር “ብሔራዊ መግባባት ለዘላቂ ሰላምና ለሀገር ግንባታ” በሚል መሪ ሐሳብ የምክክር መድረክ አካሄዷል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ረታ፤ የሃይማኖት ተቋማት ለሀገር ግንባታ፣ ለዜጎች አብሮነትና አንድነት መጠናከር ከፍተኛ ሚና አላቸው፡፡
ትውልዱ በስነ-ምግባር የታነጸ እንዲሆን ከመሥራት ባሻገር ለቀጣዩ ትውልድ የምትመች ሀገር ለማስተላለፍ የጎላ ኃላፊነት አለባቸው ብለዋል።
የሃይማኖት አባቶችና ተቋማት የሚያስተላልፏቸው ትምህርቶች የህዝቦችን ወንድማማችነት የሚያጎለብት፣ ሀገራዊ አንድነትንና አብሮነትን በጽኑ መሰረት ላይ የሚገነባ ታላቅ ሀብት መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
ኢትዮጵያ የብዝሃነት መገለጫ ሀገር እንደመሆኗ ብዝሃነትን በአግባቡ በማስተናገድ ለመጪው ትውልድ የምትመች ሀገር መገንባት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
ልዩነቶቻችንን ወደ ጎን ትተን፣ አብረን ቆመን ዳግማዊ አድዋን በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ እንዳጸናነው ሁሉ፤ በጋራ ተደምረን መገንባት ስንችል ትናንት ዋጋ የተከፈለላት ሀገር ማቆም እንችላለን ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ምክትል ጸሐፊ ሼኽ አብዱልሐሚድ አህመድ በበኩላቸው፤ የሃይማኖት ተቋማት በማህበረሰቡ ውስጥ ያላቸው ተጽዕኖ አብሮነት ለማጠናከር ትልቅ አቅም አላቸው ብለዋል።
መልካም እሴቶችን ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ ቁልፍ መሰረቶች መሆናቸውን በመግለጽ፤ አንድነትን ማጠናከር የሚያስችሉ በጎ ተግባራትን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡