የተፈጥሮ ማዳበሪያ በመጠቀማቸው ምርታማነታቸው ማደጉን የቃሉ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
የተፈጥሮ ማዳበሪያ በመጠቀማቸው ምርታማነታቸው ማደጉን የቃሉ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ
ቃሉ ፤ ጥቅምት 6/2019 (ኢዜአ)፦ የተፈጥሮ ማዳበሪያን በመጠቀም የመሬት ለምነትን በመጨመራቸው ምርታማነታቸው በተጨባጭ ማደጉን በደቡብ ወሎ ዞን የቃሉ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ።
የወሎ ዩኒቨርሲቲ በደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ ወረዳ የአፈር ለምነትን በመጠበቅ ምርታማነትን ለማሳደግ ያከናወናቸው የተለያዩ ተግባራትን ባለድርሻ አካላት ጎብኝተዋል።
የቃሉ ወረዳ የ021 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አብዱራህማን ሳኒ እንደገለጹት፣ በዩኒቨርሲቲው እገዛ የመሬታቸውን የአፈር ለምነት በመጠበቅ ምርታማነታቸውን እያሳደጉ ነው።
ምርታማነታቸው በማደጉም የምግብ ዋስትናቸውን ከማረጋገጥ ባለፈ ለገበያ የሚተርፍ ምርት ለማምረት እንደቻሉም ገልጸዋል።
በተሰጣቸው ስልጠና ተጠቅመው በአፈርና ውሃ ጥበቃና በተፈጥሮ ማዳበሪያ በመጠቀም የመሬታቸውን የአፈር ለምነት በዘላቂነት መጨመር እንደቻሉ አስረድተዋል።
በዚህም ቀደም ሲል በግማሽ ሄክታር ማሳቸው ላይ ማሽላን በመዝራት ያገኙት የነበረውን አራት ኩንታል ምርት በሶስት እጥፍ ማሳደግ መቻላቸውን ተናግረዋል።
«ከባለሙያዎች ባገኘነው ምክርና ስልጠና የመሬታችንን የአፈር ለምነት በመጠበቅ ምርታማነታችንን ማሳደግ ችለናል» ያሉት ደግሞ የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር መሀመድ ሰይድ ናቸው።
የአፈር ለምነትን እንዴት መጠበቅ እንዳለብን ባገኘነው ግንዛቤ ምርታማነታችንን በማሳደግ ተጨባጭ ውጤት አምጥተናል ብለዋል።
የተፈጥሮ ሀብት ልማትን በመጠበቅ፣ የተፈጥሮ ማዳበሪያንና የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በምግብ ራሳችንን ከመቻል አልፈን ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ ሆነናል ነው ያሉት።
በዘንድሮው መኸርም ግማሽ ሄክታር ማሳቸውን የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ በማከናወን የተፈጥሮ ማዳበሪያ ተጠቅመው ካለሙት ማሽላ 25 ኩንታል ምርት እንደሚጠብቁም ገልጸዋል።
በወሎ ዩኒቨርሲቲ ግብርና ኮሌጅ የአፈር ሳይንስ መምህርና ተመራማሪ አሊ ሰይድ በበኩላቸው፤ ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በመቀናጀት በተሻሻለ አሰራር ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው።
የተቀናጀ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ በማከናወን፣ የተፈጥሮ ማዳበሪያና ቨርሚኮምፖስት ተጠቅመው በሚዘሩት ሰብል በሽታንና ድርቅን በመቋቋም ከፍተኛ ምርት እያገኙ መሆኑን ገልጸዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አህመድ ጋሎ በበኩላቸው፤ አርሶ አደሩ የአፈር ለምነትን በመጠበቅ ምርታማነቱን እንዲያሳድግ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
ለዚህም ከዩኒቨርሲቲዎች፣ ከምርምር ተቋማት፣ ከድርጅቶችና ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በዞኑ በዘንድሮው መኸር በቴክኖሎጂና በተሻሻለ አሰራር ከለማው 433 ሺህ ሄክታር መሬት ከ15 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል።
በጉብኝቱ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የዞን፣ የወረዳ፣ የምርምር ተቋማት አመራሮች፣ ተመራማሪዎች፣ አርሶ አደሮችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።