ባለአደራ አስተዳደሩ የክልሉን ህዝብ ሰላምና ልማት በዘላቂነት ለማስጠበቅ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል - ኢዜአ አማርኛ
ባለአደራ አስተዳደሩ የክልሉን ህዝብ ሰላምና ልማት በዘላቂነት ለማስጠበቅ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 6/2019 (ኢዜአ)፦የትግራይ ክልል የፌዴራል መንግሥት ባለአደራ አስተዳደር የክልሉን ህዝብ ሰላምና ልማት በዘላቂነት ለማስጠበቅ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል ሲሉ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) ሊቀ መንበር አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) አስታወቁ።
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 62 (9) እና በዐዋጅ ቁጥር 359/1995 አንቀጽ 14/2/ለ/ መሠረት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም ባስተላለፈው ውሳኔ እና ለሚኒስትሮች ምክር ቤት በሰጠው ሥልጣን መሠረት፣ የኢፌዴሪ መንግሥት የትግራይ ክልልን የሚያጸና ውሳኔ ወስኗል።
በዚህም ይህ የትግራይ ክልል የፌዴራል መንግሥት ባለአደራ አስተዳደር ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት ትግራይን የሚያስተዳድር ይሆናል።
የባለአደራ አስተዳደሩ በሚያከናውናቸው ሁሉም ተግባራት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች፣ የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት፣ የትግራይ ሕዝብን መሠረታዊ ጥቅሞች መሠረት ማድረግ እንዳለበት ተመላክቷል።
በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት እስከሚቋቋም ድረስ የክልሉን የዕለት ተዕለት አገልግሎቶች ከማቅረብና ለቀጣይ ምርጫ አስቻይ ሁኔታዎችን ከመፍጠር በዘለለ ረዘም ያለ ስትራቴጂያዊ አንድምታ ባላቸው ጉዳዮች ላይ እንደማይንቀሳቀስም ተገልጿል።
ባለአደራ አስተዳደሩም ተግባሩን ከፌዴራል መንግሥት በሚሰጠው አቅጣጫ እና መመሪያ መሠረት ያከናውናል ነው የተባለው።
ከዚህ ጋር በተያያዘ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀ መንበር አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ የፌዴራል መንግስት የትግራይ ክልልን ለስድስት ወራት የሚያስተዳድር አካል መመስረቱ አስፈላጊ እና አዎንታዊ እርምጃ ነው።
የፌዴራል መንግስት በክልሉ ሁለንተናዊ ለውጥ እንዲመዘገብ ለሰጠው ትኩረት አድናቆታቸው ገልፀው፤ ባለአደራ አስተዳደሩ የትግራይ ክልልን ህዝብ ሰላምና ልማት በዘላቂነት ለማስጠበቅ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብለዋል።
የአስተዳደር አባላትም የትግራይን ህዝብ ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ ስራቸውን በታታሪነት በመከወን ሀላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ጠይቀው፤ የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጥብቅ ቁጥጥር ሊደረግበት እንደሚገባም ገልጸዋል።
ለባለአደራ አስተዳደሩ የተሰጡትን ቁልፍ ኃላፊነቶች የምርጫ ዝግጅት ማካሄድ፣ ሰላምን ማረጋገጥ፣ የመንግስት መዋቅሮችን መልሶ መዘርጋት፣ መሰረተ-ልማቶችን መጠገን እና ተፈናቃዮችን መመለስን ጨምሮ በስኬት ለመወጣት ከፍተኛ ዲሲፕሊን እና ግልጽነት ሊኖር ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
ፓርቲያቸው ትዴፓ ለትግራይ ክልል ህዝብ ሰላም፣ ልማት እና ህገ-መንግስታዊ ስርዓት መረጋገጥ ከህዝቡ ጎን በመቆም አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።