ቀጥታ፡

ለህዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በተጨባጭ ምላሽ ለመስጠት ጥረት እየተደረገ ነው

ደብረ ብርሃን ፤ ጥቅምት 6/2019 (ኢዜአ)፦ለህዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በተጨባጭ ውጤት ምላሽ ለመስጠት በየደረጃው ያለ አመራር በትጋት ለመስራት ዝግጁ መሆኑን የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር አስታወቀ።

በህዝብ ይሁንታ የተመረጠው ብልጽግና ፓርቲ አዲስ መንግስት መስርቶ ለህዝብ የገባውን ቃል ለመፈፀም በተደመረ አቅም ወደ ስራ መግባቱ ይታወቃል።

የመደመር መንግስት የህዝብን የልማት፣ የመልካም አስተዳደር፣ የአገልግሎት ፍላጎት ማሳካት ብሎም የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን ማድረግ የሚል አቋም ይዞ እየሰራ ይገኛል።

በየደረጃው ያለ የመንግስት አመራርም ህዝብን በማስተባበር ለህዝብ ተጠቃሚነት፣ ለሀገር ልማትና ለትውልድ የምትተርፍ ሀገር የመገንባት አደራ ተረክቦ ወደ ስራ ገብቷል።

ከዚህ አንፃር በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የተያዙ እቅዶችንና ተግባራዊ እንቅስቃሴዎችን በተመለከተ የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ተክለየስ በለጠ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በማብራሪያቸውም  ለህዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በተጨባጭ ውጤት ምላሽ ለመስጠት በየደረጃው ያለ አመራር በትጋት ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በዚሁ መሰረትም የህዝብን የልማት፣ የሰላምና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች መሰረት ያደረጉ ተግባራዊ ስራዎች ተጀምረዋል ብለዋል።

በዞኑ ያሉ እምቅ ሃብቶችን በማልማትና ምርታማነትን በማሳደግ ከተረጅነት የመውጣትና በምግብ ራስን የመቻል ጥረት ትኩረት የተሰጠው መሆኑን አንስተዋል።

በተለይም የግብርና፣ የኢንዱስትሪ፣ የማእድን፣ የቱሪዝምና የዲጅታል ዘርፉን መሰረት በማድረግ ለህዝብ ተጠቃሚነት አመራሩ በትኩረት የሚሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የመደመር መንግስት መርህ ልማትን ማረጋገጥ፣ ህዝብን ተጠቃሚ ማድረግና የሀገርን ብልጽግና እውን ማድረግ መሆኑን አንስተው በዞኑ በዚሁ መልኩ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ይገኛሉ ብለዋል።

በዞኑ በተያዘው በጀት ዓመት ለ123 ሺህ ወጣቶች በተለያዩ ሴክተሮች የስራ እድል የመፍጠር ግብ ተይዞ እየተሰራ መሆኑንም ለአብነት ጠቅሰዋል።

የከተሞችና የገጠር ኮሪደር ልማት፣ የሰው ተኮር ፕሮጀክቶች ግንባታና የግብርና ስራዎችን በተቀናጀ መልኩ ለመስራት ርብርብ ይደረጋልም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም