ቀጥታ፡

በአዳማ ከተማ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከ18 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚ የስራ ዕድል ተፈጥሯል

አዳማ ፤ ጥቅምት 6/2019 (ኢዜአ)፦በአዳማ ከተማ አስተዳደር በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከ18 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚ የስራ ዕድል መፈጠሩን የከተማዋ የስራ ዕድል ፈጠራና ክህሎት ጽሕፈት ቤት ገለፀ።

የአዳማ ከተማ የስራ ዕድል ፈጠራና ክህሎት ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ አብዱልቃድር ጠይብ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በተያዘው በጀት ዓመት ከ70ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚ የስራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ ወደ ተግባር ተገብቷል።


 

በዚህም የከተማዋን ዜጎች የስራ አጥነት ችግር ከመቅረፍ ባለፈ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ታልሞ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በተያዘው የበጀት ዓመት 70ሺህ 565 ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚ የስራ ዕድል ለመፍጠር አቅደናል ያሉት አቶ አብዱልቃድር፤ ከዚህ ውስጥ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከ18ሺህ በላይ ለሚሆኑት የስራ ዕድሉ መፈጠሩን ገልጸዋል።

ወደ ስራ የገቡ ዜጎችም ተገቢውን የስራ ክህሎትና ዕውቀት እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ የከተማዋ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች እንዲሁም ኢንዱስትሪዎች ተገቢውን የክህሎት ስልጠና እንዲሰጡ እያደረግን ነው ብለዋል።

የስራ ዕድል ከተፈጠረባቸው መስኮች መካከል ጨርቃጨርቅ፣ የአገልግሎት ዘርፍ፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ የምግብ ዘይት ምርት፣ ብረታ ብረትና እንጨት ስራ፣ ንግድ፣ የወተት ላሞችና ዶሮ እርባታ፣ የንብ ማነብ እንዲሁም የሰብል ልማት ይገኙበታል ብለዋል።


 

ለዚሁ ተግባር እስካሁን ከቀረበው 3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ውስጥም 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን የሚሆነው ብድር በማህበር ለተደራጁ ኢንተርፕራይዞች መሰጠቱን ተናግረዋል።

በተጨማሪም የማሽን ሊዝ አቅርቦት ለማሳለጥ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።

የተፈጠረው የስራ ዕድል የዜጎችን የስራ አጥነት ችግር  ከመቅረፍ ባለፈ  ገበያን ከማረጋጋት አንፃር የጎላ ሚና እየተጫወተ ይገኛል ነው ያሉት።


 

የስራ እድሉ ከተፈጠረላቸው ዜጎች መካከል የደመኮ ጨርቃጨርቅ ማህበር ስራ አስኪያጅና አባል ወጣት አዲሱ ብስራት እንደገለጸው፤ በተያዘው በጀት ዓመት በጨርቃጨርቅ ስራ በማህበር ተደራጅተው ወደ ስራ ገብተዋል።

በአሁኑ ወቅት የተለያዩ አልባሳት እያመረቱ መሆኑን ገልጾ፤ ለአዳማ እግር ኳስ ክለብ፣ ለተማሪ የደንብ ልብስ፣ ለጤና ባለሙያዎች የደንብ ልብስና ሌሎች የስፖርት ክለቦች ማሊያዎችን በጥራት እያመረቱ መሆኑን ተናግረዋል።

ከባንክ በብድር ያገኙትን ጨምሮ ከ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ካፒታል ወደ ስራ ገብተው ከ40 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ተጨማሪ የስራ ዕድል መፍጠራቸውንም ገልጿል።


 

ቦንሶ በቀለ በበኩሉ፤ በተያዘው የበጀት ዓመት በአስተዳደሩ በተመቻቸላቸው የስራ ዕድል በመጠቀም ወደ ስራ መግባታቸውን ተናግሯል።

በተለይም የቤተሰብ አቅምን በማሰባሰብና የሊዝ ማሽን ድጋፍ በማግኘት በቀን ከ700 ኩንታል በላይ የበቆሎ ዱቄት የሚያመርት ፋብሪካ በማቋቋም 49 ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚ እንዲሁም 13 ለሚሆኑት ደግሞ ጊዜያዊ የስራ ዕድል መፈጠሩን ገልጿል።

በተለይም ከአስተዳደሩ ብድርና የሊዝ ማሽን ድጋፍ ከማግኘቱም ባለፈ የፋብሪካ መገንቢያ መሬት በነፃ በማግኘቱ ፈጥኖ ወደ ስራ እንዲገባ ማስቻሉንም ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም