ቀጥታ፡

በክልሉ የታዳጊ ሴቶችን መብትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

ባህርዳር፤ ጥቅምት 6/2019 (ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ያለእድሜ ጋብቻን በመከላከልና የታዳጊ ሴቶችን መብትና ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ለነገ ሀገር ግንባታ መሰረት ለመጣል በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) ገለጹ።

ዓለም አቀፍ የታዳጊ ሴቶች ቀን ክልላዊ ማጠቃለያ የውይይት መድረክ «የታዳጊ ሴት ልጆች ህልም፤ የኢትዮጵያ የነገ ተስፋ» በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል።


 

በወቅቱም የዘርፍ አስተባባሪዋ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ታዳጊ ሴት ልጆች ትምህርትን ጨምሮ ሌሎች በማህበራዊና በኢኮኖሚያዊ ዘርፍ መብታቸውና ጥቅማቸው እንዲጠበቅ በማድረግ ለነገ የትውልድ ግንባታ መሰረት መጣል ይገባል።

ታዳጊ ሴቶች ተምረውና አውቀው የቀጣይ ህይወታቸውን በሚተልሙበትና በራስ የመተማመን መንፈስን በሚያዳብሩበት ወቅት የሚፈጸም ጋብቻን ማስቆም የባለድርሻ አካላት ኃላፊነት መሆኑን ገልጸዋል።


 

ሴት ልጅ በታዳጊነት ዕድሜዋ በትምህርት እንድትጠነክር፣ ጤናዋ እንዲጠበቅ፣ የወደፊት ህልምና ህይወቷን በነፃነት የምትቀርጽበት ተስፋ በከንቱ እንዳይባክን መስራት ይገባናል ብለዋል።

ያለዕድሜ ጋብቻ በሴቶች ላይ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር እንዲሁም የጤና እክል ከማድረሱም በላይ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ እያደረሰ ያለውን ከፍተኛ ጉዳት ለመግታት መስራት የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት መሆኑን ተናግረዋል።

የክልሉ ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ብርቱካን ሲሳይ በበኩላቸው፤ ታዳጊ ሴቶች በለጋ ዕድሜያቸው ተምረውና አውቀው የቀጣይ ህይወታቸውን እንዲመሩ ከአጋርና ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እየተሰራ ነው ብለዋል።


 

በርካታ ልጃገረዶች ተምረው ህልማቸውን እንዳይኖሩ የልጅነት ጋብቻ እንቅፋት እንደሆነባቸው ጠቁመው፣ ይህንን ችግር ለማስወገድ የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ ሥራ ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።

በአዊ ዞን እንጅባራ ከተማ የአገው ምድር 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ የነበረችውና  በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበችው ህዳሴ ዘመኑ በበኩሏ፤ በታዳጊነት እድሜዋ ያጋጠማትን ፈተና ተቋቁማ በመማሯ በ12ኛ ክፍል ፈተና 583 ውጤት በማምጣት ዩኒቨርሲቲ መግባቷን ተናግራለች።


 

ባስመዘገበችው ውጤትም በዛሬው ዕለት ለመሸለም በመብቃቷ ለሌሎች ታዳጊ ሴት ተማሪዎች መልካም ተሞክሮ እንደሚሆናቸው ገልጻለች። 

በመድረኩም በ2018 የትምህርት ዘመን በ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡ ሴት ተማሪዎች የማበረታቻ ሽልማትና እውቅና ተሰጥቷል።

በክልላዊ ማጠቃለያ በዓሉ ላይ የክልልና የዞን ከፍተኛ አመራሮች፣ ታዳጊ ሕፃናትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም