የአፍሪካን ችግር በአፍሪካውያን የመፍታት ጥረት - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካን ችግር በአፍሪካውያን የመፍታት ጥረት
በእንግዳው ከፍያለው ከባህርዳር ኢዜአ
የጣና ፎረም የአፍሪካን ችግር በአፍሪካውያን እውቀት፣ የአመራር ጥበብና እሴት የመፍታት ዓላማን ሰንቆ የተቋቋመ ነው።
ፎረሙ በዋናነት በአፍሪካ ሰላምና መረጋጋትን ማስፈን፣ ቀጣይነት ያለው እድገት ማስመዝገብ፣ ህገ ወጥ የገንዘብና የሰዎች ዝውውርን መግታትና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በመምከር የመፍትሄ ሃሳቦችን በማመንጨት ለአፍሪካ ህብረት መሪዎች ጉባኤ በማቅረብ ችግሮች እንዲፈቱ ያደርጋል።
በተፈጥሮ ጸጋ በበለጸገችው የባህርዳር ከተማ የተመሰረተው ፎረሙ ዘንድሮም “በአፍሪካ የሰላም መንገዶች፣ የኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነትና የጂኦፖለቲካ ለውጥ” በሚል መሪ ሃሳብ ይካሄዳል።
ከጥቅምት 13-15 ቀን 2019 ዓ.ም የሚካሄደው ፎረሙ የኢንዱስትሪ እድገትና ነጻነትን ማረጋገጥ፣ በዘርፉ ዘላቂነት ያለው መልካም አስተዳደር ማስፈን፣ አካታች የዲጅታል ትራንስፎርሜሽን፣ አፍሪካዊነትን የተላበሱ ተቋማትን መገንባትና ማጠናከር እንዲሁም ቀጠናዊ ትስስርና የሃብት ዝርፊያን ማስቆም በሚሉ ዋና ጉዳዮች ላይ በመምከር የመፍትሄ አቅጣጫ ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል።
በፎረሙ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች፣ የቀድሞ ፕሬዝዳንቶች፣ ምሁራንና ዲፕሎማቶች እንደሚሳተፉም ይጠበቃል።
የፎረሙ የመወያያ ነጥቦች የአፍሪካ ህብረት በ2063 ያስቀመጠውን አህጉራዊ ግብ ለማሳካት መንገድ የሚጠርጉና መደላድል የሚፈጥሩ መሆናቸውን ከመሪ ሀሳቡና አጀንዳዎቹ መገንዘብ ይቻላል።
የባህርዳር ከተማ ዘንድሮ ለ12ኛ ጊዜ የሚካሄደውን የጣና ፎረም ጉባኤ ለማዘገጃት የሚያስችላትን ዝግጅት አጠናቃ እንግዶችን ለመቀበል እየተጠባበቀች ነው።
ፎረሙን ለመታደም ወደ ባህር ዳር የሚመጡ እንግዶችም የጣና ሃይቅንና በውስጡ የሚገኙ ደሴቶችን፣ በከተማዋ የተገነባውን የኮሪደር ልማት፣ አዲሱን የአባይ ድልድይና እንደ ጭስ አባይ ያሉ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ የመስህብ ሃብቶችን በመጎብኘት መልካም ቆይታ ይኖራቸዋል።
ለዚህም ሆቴሎችና ሪዞርቶች ፈጣንና ዘመናዊ ጀልባዎችን በማዘጋጀት በጣና ሃይቅ ውስጥ የሚገኙ ገዳማትንና ሌሎች የመስህብ ስፍራዎችን ለማስጎብኘትና በሃይቁ ላይ ሽርሽር ለማካሄድ ተዘጋጅተው እየተጠባበቁ ነው።
የአማራ ክልል መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ አባይ መንግስቴ ፎረሙን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ ፎረሙን በመጠቀም የመስህብ ሃብቶችን በማስተዋወቅና የአካባቢውን ብሎም የሀገሪቱን ገጽታ በመገንባት የውጭ ሀገራት ጎብኞችን ለመሳብ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በሀገር በቀል ኢኮኖሚው ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች አንዱ የሆነውን የቱሪዝም ዘርፍ ይበልጥ በማልማትና በማስተዋወቅ ለመጠቀም ፎረሙ መልካም እድል ይዞ መምጣቱንም አስረድተዋል።
በከተማዋ የሚገኙ የሆቴል አመራሮችም የእንግዶች ማረፊያ፣ የመሰብሰቢያና የመመገቢያ አዳራሽ፣ የኢንተርኔትና ሌሎች አስፈላጊ የአገልግሎት መስጫዎችን ማሟላታቸውን አመልክተዋል።
በፎረሙ ለመሳተፍ የሚመጡ እንግዶችን በኢትዮጵያዊ መልካም መስተንግዶ በማስተናገድ የቆይታ ጊዜያቸውን ለማራዘም እንዲሁም ቆይታቸውን አይረሴ ለማደረግ የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።