የኩታገጠም አሰራር በመከተልና የግብርና ቴክኖሎጂዎችን መጠቀማችን ተጠቃሚ አድርጎናል - ኢዜአ አማርኛ
የኩታገጠም አሰራር በመከተልና የግብርና ቴክኖሎጂዎችን መጠቀማችን ተጠቃሚ አድርጎናል
ደብረማርቆስ ፣ጥቅምት 6/2018 (ኢዜአ)፡-የኩታ ገጠም አሰራር እና ሌሎች የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ተግባራዊ ማድረጋችን ተጠቃሚ አድርጎናል ሲሉ በምስራቅ ጎጃም ዞን የሚገኙ አርሶ አደሮች ገለጹ።
በምስራቅ ጎጃም ዞን በባሶ ሊበን፣ በአዋበልና በደጀን ወረዳዎች የሰብል ጉብኝት ተካሂዷል።
የባሶ ሊበን ወረዳ የልምጭም ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ባየ አበበ እና ቄስ አስማረ ብርሃኔ፤ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ተግባራዊ ያደረጉት የኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ ምርታማ በመሆን ይበልጥ ተጠቃሚ አድርጎናል ብለዋል።
የአስተራረስ ዘዴው ከአጎራባች አርሶ አደሮች ጋር በተመሳሳይ ቀን በመዝራት፣ ግብዓት በመጠቀም፣ በጋራ በማረምና ተባይን ለመከላከል ሰፊ አስተዋጽኦ እንዳበረከተላቸው ገልፀዋል ፡፡
በተጨማሪም የደረሰ ሰብልን በኮምባይነር በጋራ ለመሰብሰብ እና ለመውቃት የሚያስችል በመሆኑ የምርት ብክነትን ለመቀነስ እንዳስቻላቸውም ነው የጠቀሱት።
በመሆኑም የአስተራረስ ዘዴውን ተከትለን ማሳችንን በማልማታችን አድካሚ የነበረውን የማረስ፣ የመሰብሰብና የመውቃት ሥራ አቅልሎናል ነው የሚሉት።
በክረምቱም በኩታ ገጠም የአመራረት ዘዴ የዘሩት ስንዴ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ነው አርሶ አደሮቹ ለጎብኝዎቹ የገለጹት።
የአዋበል ወረዳ የእነቢ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ደረጀ ገላው በበኩላቸው፤ የኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴን መከተል መጀመሬ ከራሴ አልፎ ለገበያ የሚተርፍ ምርት ለማምረት አስችሎኛል ነው የሚሉት።
በተያዘው የመኸር ወቅትም በአንድ ሄክታር ማሳቸው ላይ በኩታ ገጠም ያለሙት የጤፍ ቡቃያም ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ሰብሉ በጥሩ ቁመና ላይ እንዲገኝ ማድረጉን ነው የገለጹት።
በምክትል ርእሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ ድረስ ስሃሉ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ የኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ውጤት እያስገኘ ነው።
ለዚህም በምስራቅ ጎጃም ዞን የአስተራረስ ዘዴውን ተጠቅመው ጤፍ እና ስንዴ ያለሙ አርሶ አደሮች ያገኙት ውጤት ጥልቅ ማሳያ እንደሚሆን ነው ያስረዱት።
የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ መስፍን አበጀ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በክልሉ በተያዘው የምርት ዘመን በዘር ከተሸፈነው ከ5 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ውስጥ ከ60 በመቶው በኩታ ገጠም መልማቱን ገልጸዋል።
የአስተራረስ ዘዴው ቀደም ሲል በሄክታር ይመረት የነበረውን 36 ኩንታል ምርት ወደ 42 ኩንታል ለማሳደግ እንዳስቻለም አመለክተዋል።
በቀጣይም አዳዲስ አሰራሮችንና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ፣ ለገበያ የሚተርፍ ምርት ለማምረት ሥራውን በተሻለ መንገድ ለማሳደግ ወደ ሥራ መገባቱን አንስተዋል።