ቀጥታ፡

ባህል እየሆነ የመጣው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 6/2019 (ኢዜአ)፦ በመዲናዋ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ባህል እየጎለበተ በመምጣቱ በመርሃ ግብሩ የሚሳተፉ ዜጎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኅብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

የመደመር መንግሥት የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እያከናወናቸው ከሚገኙ ተግባራት በተጨማሪ የማህበረሰቡ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንዲጠናከር ባለፉት ዓመታት ተቋም ከማቋቋም ጀምሮ በርካታ ስራዎችን ሲሰራ ቆይቷል።

በዚህም ዜጎች በበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች በንቃት እንዲሳተፉ ከማድረግ ባሻገር በመላ ሀገሪቱ የበርካታ ዜጎች ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን መፍታት ያስቻሉ ውጤታማ ስራዎች ተሰርተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለበጎ ፈቃድ አገልግሎት በሰጠው ትኩረት ራሱን የቻለ ተቋም በማቋቋም በዘርፉ ውጤታማ ስራዎች እንዲሰሩ በማድረግ በኩል ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ተቋም እየሆነ መጥቷል።

ይህ ተቋም የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶችን በስፋት በማከናወን የሀገር ባለውለታዎች እና እጅ አጠር የከተማዋ ነዋሪዎች ማህበራዊ እና ኢኮኖመሚያዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ እያደረገ ይገኛል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኅብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አስራት ንጉሴ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በመዲናዋ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ባህል እያደገ በመምጣቱ የሚሳተፉ ነዋሪዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል፡

የበጎ ፈቃድ የማህበረሰብ አገልግሎቱ ከሰኔ 1 ቀን 2018 ዓ.ም እስከ መስከረም 30 ቀን 2019 ዓ.ም ድረስ ለተከታታይ ወራት ሲተገበር መቆየቱንም አንስተዋል።

በክረምቱ ወቅት ከተተገበሩት 18 የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ፕሮግራሞች መካከል የቤት ግንባታ፣ የቤት እድሳት፣ የደም ልገሳ፣ የአረንጓዴ ዐሻራ እና ማዕድ ማጋራት በዋናነት ተጠቃሽ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎቱ 9 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር የሚደርስ ሃብት በገንዘብ፣ በእውቀትና በጉልበት በማሰባሰብ ወደ ሶስት ሚሊየን የሚጠጉ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን አስታውሰዋል፡፡

በተከናወኑ ውጤታማ ተግባራት 2 ነጥብ 6 ሚሊየን የማህበረሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ 10 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር የሚገመት ሀብት በገንዘብ፣ በእውቀትና በጉልበት ማሰባሰብ መቻሉን ተናግረዋል።

በዚህም ከሶስት ሚሊየን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ጠቁመው ውጤቱ በከተማዋ በበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ላይ በንቃት የሚሳተፉ ነዋሪዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ያሳያል ብለዋል።

ውጤቱ ማህበረሰቡ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ባህል እያደረገ በመምጣቱና ንቁ ተሳትፎ በማድረጉ የተመዘገበ መሆኑንም ኮሚሽነሯ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መንግሥት ከሚያከናውናቸው መደበኛ የልማት ተግባራት ጎን ለጎን ትልቅ የልማት እና የዜጎች ተጠቃሚነት ማረጋገጫ አቅም እየሆነ መምታቱንም አመላክተዋል።

በቀጣይም በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ የሚሳተፉ የከተማዋ ነዎሪዎች ቁጥር እና የሚሰበሰበውን ሀብት በላቀ ደረጃ ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራም ተናግረዋል።

በዚህም ለማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ችግሮች በመቅረፍ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል፡፡


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም