የመደመር ዲፕሎማሲ- ኢትዮጵያን የዓለም አቀፍ ትብብር ማዕከል ያደረገው የ‘4A’ መርህ እመርታ - ኢዜአ አማርኛ
የመደመር ዲፕሎማሲ- ኢትዮጵያን የዓለም አቀፍ ትብብር ማዕከል ያደረገው የ‘4A’ መርህ እመርታ
በቁምልኝ አያሌው (ኢዜአ)
ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ
ኢትዮጵያን የዓለም አቀፍና አህጉራዊ የዲፕሎማሲ መድረክ የረጅም ዘመናት ታሪካዊ ሚና እና ስትራቴጂያዊ ስፍራ ይሰጣታል። በ1945 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ቻርተርን ከፈረሙት መሥራች አባላት አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ በ1963 የወቅቱ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የአሁኑ የአፍሪካ ሕብረት ሲመሰረትም የአህጉሪቱን አንድነት በማጠናከር ቁልፍ ሚና ተወጥታለች። የአፍሪካ ሕብረት ዋና መሥሪያ ቤትን በመዲናዋ ማስተናገዷም አዲስ አበባን የአፍሪካ የፖለቲካና ዲፕሎማሲ ዋነኛ ማዕከል አድርጓታል።
ዛሬም አዲስ አበባ የአፍሪካ መሪዎች፣ የዲፕሎማቶችና የዓለም አቀፍ ተቋማት መገናኛ ከመሆኗም በላይ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ አጀንዳዎች የሚመከሩባትና የሚቀረጹባት ወሳኝ የዲፕሎማሲ መድረክ ሆና ቀጥላለች። ይህ ታሪካዊ ሚና ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምን በማስጠበቅ የኢኮኖሚ ትብብርን ለማስፋትና ቀጣናዊ የሰላምና ደኅንነት ጉዳዮች ተሳትፎ በማጎልበት ሰፊ ዕድል ፈጥሯል።
የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ በታሪካዊ እርሾ በመመስረት ብሔራዊ ጥቅምና ፍላጎትን ከጋራ ተጠቃሚነት መርህ ጋር በማጣጣም የሚጓዝ ነው። የመደመር መንግሥትም ይህንን ታሪካዊ መሰረት መነሻነት በማድረግ ዲፕሎማሲን ከመደበኛ የውጭ ግንኙነት ተግባር ወደ ተጨባጭ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የደኅንነት ውጤት የሚያሸጋግር አካሄድ እየተከተለ ይገኛል።
የመደመር መንግሥት ዲፕሎማሲም ከውስጥ የሚነሳ ቅድሚያ ለጎረቤት የሚሰጥ ለአህጉሪቷ አፍሪካ፣ ለዓለም አቀፍ የሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን የትብብር አድማስን የሚያሰፋ በገቢር ነበብ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ የሚመራ ነው። ገቢር ነበብ የዲፕሎማሲ አካሄዱም በአራት ዋና ዋና መሰረታዊ መርሆዎች ማለትም ንቁ ተሳትፎን ማረጋገጥ (Active)፣ አማራጭ የአጋርነት መስመሮችን ማስፋት (Alternative)፣ ከተለዋዋጭ ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች ጋር መላመድ (Adaptive) እና ዓለም አቀፍ አጀንዳዎችን በመቅረጽ ላይ የበለጠ ሚና መውሰድ (Agenda-setting) ላይ የተመሰረተ ነው።
እነዚህ መርሆዎችም የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ የትብብር ተሳትፎ በማላቅ ብሔራዊ ጥቅሟን በማስጠበቅ ከፍተኛ ውጤት እያስገኘ ነው። የዲፕሎማሲው ዋነኛ ዓላማም በጉባኤዎች መሳተፍና ስምምነቶችን መፈራረም ብቻ አይደለም። እነዚህን ግንኙነቶች ወደ ንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ ቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የሰው ኃይል ልማትና የዜጎች ተጠቃሚነት የሚቀየር ውጤታማ የትብብር አድማስን ማስፋት ነው።
ኢትዮጵያ በ2024 የብሪክስ (BRICS) ሙሉ አባል መሆኗ የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲያዊ አጋርነቷን ለማስፋት ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ወሳኝ ምዕራፍ ነው። የብሪክስ አባልነት ኢትዮጵያ ከተለያዩ የዓለም ኢኮኖሚዎች ጋር ያላትን ትስስር ለማጠናከር፣ አዳዲስ የንግድና የኢንቨስትመንት ዕድሎችን ለመፍጠር እንዲሁም በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ላይ ያላትን ተሳትፎ ለማጠናከር ዕድል ይሰጣል።
የብሪክስ ትብብር በኢንዱስትሪ፣ በግብርና፣ በኃይል፣ በዲጂታል ኢኮኖሚና በመሠረተ ልማት ዘርፎች የጋራ ፕሮጀክቶችን ለማሳደግ አስፈላጊ መድረክ ሆኗል። በአዲሱ የልማት ባንክ አማካኝነትም ለመሰረተ ልማትና ለዘላቂ ልማት የሚውል ፋይናንስ ለማግኘት ዕድል ይፈጥራል። በአባል ሀገራት መካከል የክፍያ ሥርዓቶችን ማሻሻልና በአገራዊ ገንዘቦች የሚካሄድ ንግድን ማሳደግም የውጭ ምንዛሬ ጫናን ለመቀነስ ያግዛል።
ለኢትዮጵያ በተለይም የወጪ ንግድን ለማሳደግ፣ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርታማነትን ለማሻሻል፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማፋጠንና የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ አባልነቱ ተጨማሪ ዕድሎችን ይከፍታል። ይሁንና እነዚህ ዕድሎች ወደ ተጨባጭ ጥቅም እንዲቀየሩ በሀገር ውስጥ የምርት አቅምን ማሳደግ፣ ተወዳዳሪነትን ማጠናከርና የትብብር ስምምነቶችን በተግባር ማዋል ወሳኝ ናቸው።
ኢትዮጵያ በዓለም ንግድ ድርጅት (WTO) አባል ለመሆን የምታደርገው ጥረትና የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና (AfCFTA) ስምምነትን ለመተግበር ያላት ቁርጠኝነትም የዚሁ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ አካል ናቸው። እነዚህ ጥረቶች ለኢትዮጵያ የውጭ ገበያዎችን ለማስፋት፣ የንግድ ትስስርን ለማጠናከርና የኢንቨስትመንት ፍሰትን ለማበረታታት ዕድል ይፈጥራሉ።
የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫዎች መካከል የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም በማስጠበቅ በቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ መድረኮች ላይ አጀንዳ በመቅረጽ ላይ የበለጠ ሚና መውሰድ ይገኝበታል። በዚህ ረገድ የባሕር በርና የወደብ መዳረሻ ጉዳይ ከፍተኛ ስትራቴጂያዊ አስፈላጊነት አለው።
ኢትዮጵያ እ.አ.አ. ከ1993 ጀምሮ የባሕር በር የሌላት ሀገር ሆናለች። ይህም ለውጭ ንግዷ፣ ለወደብ አገልግሎትና ለሎጂስቲክስ ወጪ ተጋላጭነትን በማስፋት በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ውድድርና በቀጣናዊ ትስስር ላይ ተጨማሪ ጫና እየፈጠረ ይገኛል። ስለሆነም የባሕር በርና የወደብ መዳረሻ ጉዳይ ከንግድ ፍላጎት ባለፈ ከኢኮኖሚ ደኅንነት፣ ከቀጣናዊ ትስስርና ከረጅም ጊዜ ልማት ጋር የተቆራኘ የሕልውና ጉዳይ ነው።
የመደመር መንግሥት ዲፕሎማሲ ይህንን ጉዳይ በታሪክ፣ በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ በኢኮኖሚያዊ ፍላጎት እንዲሁም በቀጣናዊ ሰላምና ደኅንነት አውድ እያቀረበ ይገኛል። በተለይም ቅድሚያ ለጎረቤት የሚለው የውጭ ግንኙነት የፖሊሲ አቅጣጫም በሰላማዊ ድርድር፣ በዓለም አቀፍ ሕግና በጋራ ተጠቃሚነት (Win-Win) መርህ ላይ የተመሠረተ መፍትሔ ለማምጣት ያለውን ጽኑ አቋም ያሳያል።
የባሕር በርና የወደብ መዳረሻ ጉዳይ በሰላማዊ መንገድ መፍትሔ ማግኘቱ ለኢትዮጵያ ወጪና ገቢ የንግድና የሎጂስቲክስ አገልግሎት መሳለጥ፣ የኢኮኖሚ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግና የቀጣናዊ ትስስርን የሚያጠናክር የሕልውና ጉዳይ ነው። ከዚህ በተጨማሪም በአፍሪካ ቀንድ የንግድ፣ የኃይል፣ የውሃና የመሠረተ ልማት ትብብርን በማስፋት ቀጣናዊ ሰላምና ደኅንነትን በማረጋገጥ የጋራ ብልፅግናን እውን ማድረግ ያስችላል።
የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ በባለብዙ ወገን መድረኮች አይገደብም። ከተለያዩ ሀገራት ጋር ያለው የሁለትዮሽ ግንኙነትም ሌላኛው ቁልፍ የትብብር አድማስ ነው። ከሕንድ፣ ቱርክዬ፣ ፈረንሳይ፣ ጣሊያንና ከሌሎች ሀገራት ጋር ያላት ግንኙነት በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በቴክኖሎጂ፣ በሰው ኃይል ልማትና በደኅንነት ዘርፎች የጋራ ጥቅምን የሚያሰፋ ዕድል እየፈጠረ ይገኛል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ የተለያዩ ሀገራት መሪዎችና ባለሥልጣናት ጋር የሚያደረጉ የዲፕሎማሲ ምክክር የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያጎለብት አቅም እየገነቡ ነው። ይህም ዲፕሎማሲው ከፖለቲካዊ መግለጫዎችና ከመደበኛ ስብሰባዎች ባለፈ ለሀገር ልማትና ለዜጎች የኑሮ መሻሻል ቀጥተኛ አስተዋጽኦ ማበርከት አስቸሏል። ለአብነትም የገበያና የዜጎች የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት በማስፋት አስቻይ የንግድና ኢንቨስትመንት ምኅዳር እንዲፈጠር አድርጓል።
ኢትዮጵያ በታሪኳ ያካበተችውን የዲፕሎማሲ ልምድ በዘመኑ ከሚጠይቀው የዓለም አቀፍ የትብብር አቅጣጫ ጋር በማጣመር የብሔራዊ ጥቅሟን የምታስጠብቅበትን መንገድ ትከተላለች። በብሪክስ አባልነቷ፣ በዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን በምታደርገው ጥረት፣ በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ትግበራ ላይ ባላት ቁርጠኝነትና በሁለትዮሽ ግንኙነቶቿ ላይ በምታደርገው ጥረት ይህንን አቅጣጫ እያጎለበተ ነው።
ይህም የኢትዮጵያን የብሔራዊ ጥቅም በማስጠበቅ የሀገርን የምርት አቅም በማሳደግ፣ የኢኮኖሚ ተወዳዳሪነትን በማጠናከር፣ ለዜጎች ተጨባጭ የልማት ዕድሎችን በመፍጠርና ለቀጣናዊ ሰላም ዘላቂ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው። የ4A* የዲፕሎማሲ መርሆዎችም ተግባራዊ ውጤት ማስገኘታቸውን ቀጥለዋል።
ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ቅቡልነት ያገኘው የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄም የማይቀለበስ የሰርክ አጀንዳ ሆኗል። አጀንዳውም ዓለም አቀፍ ቅቡልነት አግኝቷል። ጥያቄውም በማያወላዳ የዲፕሎማሲ ቁርጠኝነት ምላሽ የሚያገኝ ይሆናል። ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ የሰነቀችው ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው ዘርፍ ታሪካዊ ክብሯን በዘመናዊ የትብብር አድማስ በማጠናከር የብሔራዊ ጥቅሟን በትብብርና የጋራ ተጠቃሚነት መርህ በማስከበር ለዜጎቿ የተሻለ ነገ ለመገንባት እየተጋች ነው።