ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የድህነት ቅንሳ ጥረትና ውጤቱ ምን ይመስላል?

የዘንድሮው የዓለም የድህነት ቅነሳ ቀን "ለሁሉም ደህንነቱ የተጠበቀ መኖሪያ" በሚል መሪ ሀሳብ ነገ ቅዳሜ ጥቅምት 7 ቀን 2019 ዓ.ም በመላው ዓለም ይከበራል። የመሪ ሀሳቡ ዋና አላማም መኖሪያ ቤት የሰበአዊ መብት ጉዳይ በመሆኑ የድህነት ቅነሳን እውን ለማድረግና ሰብአዊ ክብርን ለመጠበቅ ጠንካራ አቋም ይዞ መስራት እንደሚገባ ይታመናል።

በዚሁ መሰረትም የዘንድሮው የዓለም የድህነት ቅነሳ ቀን የሚከበር ሲሆን ከእለቱ ጋር በማያያዝ በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ የድህነት ቅነሳ ስትራቴጂክ ትግበራዎችን እንቃኛለን። የመደመር መንግስት ሰው ተኮር የልማት ፕሮጀክቶችንና የሀገር እድገትና ብልጽግናን መሰረት አድርጎ እየሰራ ውጤትም እያመጣ ይገኛል። 

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይፋ ተደርገው ተግባራዊ እንቅስቃሴ ከሚደረግባቸው የልማት እቅዶች (የጉባ ብስራቶች) መካከል የመኖሪያ ቤት ልማት አንዱ መሆኑ ይታወቃል።

በዚሁ መሰረትም በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቤቶችን በመገንባት የመኖሪያ ቤትን ችግር ለመፍታት ከፍተኛ ርብርብ የሚደረግ ይሆናል። የቤቶች ልማት ፕሮግራም ከተሞች ካላቸው ፈጣን የህዝብ ዕድገት እና የነዋሪዎች የቤት ፍላጎት ጋር ተያይዞ በትኩረት እየተሰራበት መሆኑም ይታወቃል። በመሆኑም የልማት ኢንሸቲቩ ኢትዮጵያ ለደህነት ቅነሳ የምታደርገውን ጥረት የሚያመላክት ነው።

ከቤት ልማት በተጨማሪ የመጠጥ ውኃ፣ የኤሌክትሪክ፣ የመንገድ እና ሌሎችም መሰረተ ልማቶችን በማስፋፋት ረገድም ትልቅ እመርታ ተመዝግቧል። የግንባታ ግብአት አቅርቦትን በማጠናከር በኩል የሀገር ውስጥ የግንባታ እቃዎች (ሲሚንቶ፣ ብረት እና ሌሎች ግብአቶች) አቅርቦትን ለማሳደግ እና የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን አቅም ለማሳደግ አስችሏል። በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የቤቶች ልማት ፕሮግራም ከመንግስት ተኮር ብቻ የልማት አካሄድ ወጥቶ የግል ሴክተሩን ባሳተፈ መልኩ መከናወኑን ቀጥሏል።


 

ከከተሞች ልማት ባሻገር በገጠር ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የገጠር ኮሪደር ልማት ፕሮግራም የአርሶ እና አርብቶ አደሮች ዘመናዊ የአኗኗር ዘይቤ እንዲከተሉ መሰረት አያኖረ መሆኑ ይታወቃል።

የገጠር ሞዴል መንደሮች ግንባታ የተበታተነ የገጠር አኗኗር ዘይቤ በአንድ ማዕከል በማሰባሰብ የመጠጥ ውኃ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል (እንዲሁም ታዳሽ ኃይል እንደ ባዮጋዝ)፣ የጤና አገልግሎት፣ የትምህርት እድሎችን ለማስፋትና ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ትልቅ አቅም ሆኗል። በድምሩ የገጠርና ከተሞችን ትስስር በማጠናከር የዜጎችን አኗኗር የተሻለ ማድረግና ድህነትን ለማሸነፍ የሚደረግ ትግል እመርታ እየተመዘገበበት ይገኛል።

የድህነት ቅነሳ ጉዳይ የገቢ ማነስ ብቻ ሳይሆን የምግብ ዋስትና፣ የትምህርት፣ የጤና፣ የመኖሪያ ቤት፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ፣ የሥራ ዕድል እና ሌሎችንም የሚያካትት በመሆኑ በዚሁ መሰረት ኢትዮጵያ ለድህነት ቅንሳ የተቀናጀ ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች።

ኢትዮጵያ ከፍተኛ የግብርና አቅም ያላት ሀገር ብትሆንም በአብዛሃኛው በዝናብ ላይ የተመሠረተ የግብርና ልማት፣ የምርታማነት ውስንነት፣ የገበያ ችግሮችና ሌሎችም ተያያዥ ችግሮች በዘርፉ የሚፈለገውን ያክል ውጤት ለማምጣት ፈተና ሆነው ቆይተዋል።

አሁን ላይ የበጋ መስኖ ልማትን በማስፋፋት፣ የስንዴ ምርትን በማሳደግ፣ የተሻሻለ ምርጥ ዘር እና ዘመናዊ የእርሻ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ምርታማነትን በማሳደግ ከድህነትና ከተረጅነት የመውጣት ጥረት ተጠናክሮ ቀጥሏል። የግብርና ምርቶችን ከማምረት ባሻገር የማከማቻ፣ የማቀነባበሪያ፣ የመጓጓዣና የገበያ ትስስርን በማሻሻል የሚታዩና የሚጨበጡ ውጤቶችን ማስመዝገብ ተችሏል።

የድህነት ቅነሳ ተግባራት በሰፊ የእርሻ መሬት ላይ ብቻ ሳይወሰኑ በቤተሰብ ደረጃ የሚከናወኑ የምግብና የገቢ ማስገኛ ሥራዎችንም ማካተት ችለዋል። በመሆኑም በሌማት ትሩፋት የዶሮ እርባታ፣ የወተት ላሞች እርባታ፣ የንብ ማነብ፣ የዓሣ ምርት፣ የአትክልትና የፍራፍሬ ልማት በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናንና ለማረጋገጥና የገቢ አቅምን ለማሳደግ እያገዙ ነው። እነዚህ ሥራዎች በተለይ የመሬት ይዞታቸው ውስን ለሆኑ አርሶ አደሮች፣ ለሴቶችና ለወጣቶች ተጨማሪ የገቢ ምንጭ መሆን ችለዋል።

በድህነት ቅነሳ ረገድ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በማስፋፋት፣ የሀገር ውስጥ ምርትን በማበረታታትና የግል ዘርፉን በምርትና በአገልግሎት ዘርፎች በማሳተፍ የሥራ ዕድሎችን መፍጠር ተችሏል። በተለይም ወጣቶች በቴክኒክና ሙያ ሥልጠና በመታገዝ የሚፈለጉ ክህሎቶችን እንዲያገኙና የራሳቸውን ሥራ እንዲጀምሩ በማድረግ ገቢ እንዲያገኙ እየተደረገ ይገኛል። በመሆኑም የኢንዱስትሪ ዘርፉ ለብዙዎች የስራ እድል በመፍጠር፣ ምርታማነትንና ገቢን በማሳደግ የድህነት ቅነሳ ሁነኛ መሰረት ሆኗል።

የድህነት ቅነሳ በኢኮኖሚ እድገት ብቻ አይረጋገጥም፤ የመሠረታዊ ትምህርትን ማስፋፋት፣ የጤና አገልግሎትን ማዳረስ፣ የእናቶችና የሕፃናት ጤናን መጠበቅ፣ የንጹህ ውሃና የንጽህና አገልግሎቶችን ማሻሻል የሚገባ በመሆኑ በዚሁ መሰረት ስራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል። በተጨማሪም የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና፣ የዲጂታል ክህሎት ማስፋፋትና ከሥራ ገበያው ፍላጎት ጋር የተጣጣሙ የትምህርት ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል።

የሞባይል ገንዘብ፣ የዲጂታል ክፍያ፣ የኦንላይን ንግድና የቴክኖሎጂ መሠረት ያደረጉ አገልግሎቶች ዜጎች ከገበያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማሻሻል ያስቻለ ሆኗል። በተለይ ባንክ አገልግሎት የቁጠባ፣ የክፍያና የብድር አገልግሎቶች መመቻቸታቸው በንግድና በስራ እድል ፈጠራ ረገድ ብዙ ውጤት አምጥቷል።

የአካባቢ ሀብትን በዘላቂነት መጠቀም በተለይ ለድርቅና ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ የሆኑ ማኅበረሰቦች የኑሮ ዋስትናን ለማጠናከር አግዟል። ከዚህ አንጻር የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ የአካባቢ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የምግብ ዋስትና፣ የሥራ ዕድል ፈጠራና የድህነት ቅነሳ መሰረት ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።
 
እንደ አጠቃላይ የድህነት ቅነሳ ስራ የግብርና ምርታማነትን ከማሳደግ፣ የቤተሰብ የምግብ ዋስትናን ከማጠናከር፣ ኢንዱስትሪን ከማስፋፋት፣ የሥራ ዕድሎችን ከመፍጠር፣ ትምህርትና ጤናን ከማሻሻል፣ የተፈጥሮ ሀብትን ከመጠበቅና የማኅበራዊ ጥበቃ ሥርዓቶችን ከማጠናከር ጋር የተሳሰረ የረጅም ጊዜ ሂደት ነው። በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ትክክለኛ እቅድ ነድፋ ውጤታማ የሆነ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ላይ መሆኗን መናገር ይቻላል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም