ቀጥታ፡

በጊምቢ ከተማ መሶብ የአንድ ማዕከል ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት እያገኘን ነው

ጊምቢ፤ ጥቅምት 6/2019 (ኢዜአ)፡-በጊምቢ ከተማ መሶብ የአንድ ማዕከል ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት እያገኙ መሆኑን በምእራብ ኦሮሚያ ዞን የጊምቢ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

ነዋሪዎች ከዚህ ቀደም አገልግሎት ለማግኘት ረጅም ርቀት መጓዛቸውና በርካታ መሥሪያ ቤቶችን በማዳረስ ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውንና ገንዘባቸውን  ከማባከኑም በላይ ለቅሬታ ዳርጓቸው ቆይቷል።

በዚህም መንግሥት የህዝብን እንግልት ለማስቀረት እና ፍትሃዊ፣ ፈጣን እንዲሁም ከወረቀት ንክኪ የጸዳ አገልግሎት ለመስጠት መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በማስፋፋት ላይ ይገኛል።

ይህ አሰራር ዜጎች ጊዜያቸውን በአግባቡ ተጠቅመው ወደ ስራ ገበታቸው እንዲመለሱ በማድረግ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ላይ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡት የጊምቢ ከተማ ነዋሪዎች እንዳሉት፤ በመሶብ የአንድ ማዕከል ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት እያገኙ ነው።

ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ኮርሳ ተክሌ እንደገለጹት በአከባቢው ከዚህ ቀደም ጉዳያቸውን ለማስፈጸም የተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን በመዞር ጊዜያቸውና ገንዘባቸው ሲባክን እንደነበረ አስታውሰዋል።

በአሁኑ ወቅት በጊምቢ መሶብ በመከፈቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ጉዳያቸውን ማጠናቀቅ በመቻላቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

ግብር ለመክፈል ወደ ማዕከሉ የመጡት አቶ ኮርሳ ከወረቀት ንክኪ በጸዳ መልኩ በቴክኖሎጂ የታገዘ ቀልጣፋ አገልግሎት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ቀልጣፋ አገልግሎት በአንድ ማዕከል እንድናገኝ በማድረግ፤ ቀደም ሲል ይደርስብን የነበረውን እንግልትና ያልተገባ ወጪ አስቀርቶታል ያሉት ደግሞ ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ግርማ ቢራሳ ናቸው።


 

አገልግሎቱን በአንድ ቦታ በተሟላና በአጭር ጊዜ ውስጥ ማግኘታችን፤ የህብረተሰቡን እንግልት ከማስቀረትም ባሻገር፣ ወደ ሥራ ገበታችን ተመልሰን በሌላ ልማት ሀብት እንድናፈራ የሚያግዘን ነው ብለዋል።

ማዕከሉ ተግባራዊ መሆኑ ዜጎች የተሻለ አገልግሎት በእኩልነት እንዲያገኙ የሚያስችል በመሆኑም፣ ተግባሩ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።


 

የንግድ ፍቃድ ለማሳደስ ወደ ማዕከሉ የመጡት አቶ ዋቅጂራ ታምሩ በበኩላቸው፣ ከዚህ በፊት ከነበረው አላስፈላጊ ወጪና ምልልስ በጸዳ መልኩ የፈለጉትን አገልግሎት ማግኘት መቻላቸውን አስታውቀዋል።

የጊምቢ ከተማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ አቶ ዋቅቶሌ መልካ እንደገለጹት፣ ማዕከሉ ለህብረተሰቡ ፈጣን እና ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።


 

በማዕከሉ የአገልግሎት ተደራሽነትን ከመቀላቀል ባለፈ፣ የነበሩ ውስብስብ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን በመቅረፍ ተገልጋዮች የሚፈልጉትን አገልግሎት ከእንግልት በጸዳ መልኩ እንዲያገኙ ተችሏል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም