ከመደመር መንግሥት ጎን በመሆን ለዘላቂ ሰላምና ልማት እቅዶች መሳካት የድርሻችንን እንወጣለን -ወጣቶች - ኢዜአ አማርኛ
ከመደመር መንግሥት ጎን በመሆን ለዘላቂ ሰላምና ልማት እቅዶች መሳካት የድርሻችንን እንወጣለን -ወጣቶች
አዶላ/ነገሌ ቦረና፣ ጥቅምት 6/2019 (ኢዜአ) ፡-ከመደመር መንግሥት ጎን በመሰለፍ ለዘላቂ ሰላምና ልማት እቅዶች መሳካት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት ዝግጁ መሆናቸውን የደቡብ ኦሮሚያ ዞን ወጣቶች አስታወቁ።
ትልቅ ሀገር፤ ትልቅ ህዝብ፤ ታላቅ ርዕይ
ወጣቶች በሀገር ግንባታ፣ በሰላም ማስከበርና በልማት ስራዎች ላይ ንቁ ተሳታፊ መሆን ከቻሉ ለአንድ ሀገር ዘላቂ እድገት ወሳኝ ሚና ይጫወታል።
በተለይም የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ማጠናከር፣ የአካባቢን ሰላም ማስከበርና በኢኮኖሚ ጥረቶች ላይ መሳተፍ የዘመኑ ወጣቶች ዋነኛ ተግባር ተደርጎ ይወሰዳል።
በደቡብ ኦሮሚያ ዞን የሚገኙ ወጣቶችም ከዚህ ቀደም በተለያዩ የልማትና የሰላም ግንባታ መድረኮች ላይ ንቁ ተሳትፎ ሲያደርጉ የቆዩ ሲሆን፣ አሁን ላይ ደግሞ የመደመር መንግሥት ከያዛቸው ሀገራዊና ክልላዊ እቅዶች ጋር በመሰለፍ የአካባቢያቸውን ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ እንቅስቃሴያቸውን ማጠናከራቸውን ነው የገለጹት።
የአዶላ ከተማ ነዋሪ ወጣት ሀሰን ኡመር አዲስ የተመሰረተው የመደመር መንግስት ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ የያዘው እቅድ የሚደገፍ መሆኑን ተናግሯል።
ወጣቱ እንዳለው የባህር በር፣ የሀገር ሉዓላዊነትና ብሄራዊ ጥቅም የማስከበር ጉዳይ የትውልዱ ሁሉ መሻትና ጥያቄ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለቀጣይ አምስት ዓመታት ያስቀመጡት የሰላምና ልማት አቅጣጫ የወጣቱም እምነትና ፍላጎት በመሆኑ የሚጠበቅበት ሀላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል።
ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ በመደመር መንግሥት የተሻሻለው የዞኖችና የቀበሌ አደረጃጀትም ተስፋ ያለው ነው ያለው ወጣቱ፣ የአብሮነት፣ የሰላምና የልማት እሴቶችን ለማጽናት ከመደመር መንግሥት ጎን እንሰለፋለን ብለዋል።
የዚሁ ከተማ ነዋሪ ወጣት ረቢራ ገመዳ ባለፉት አመታት የአረንጓዴ አሻራ፣ የሌማት ትሩፋት፣ የበጋ መስኖና የስራ እድል ፈጠራ ስራዎች ወጣቱን ለስራ ያነሳሱ መሆናቸው ጠቅሶ፣ የመሰረተ ልማት ስራዎች ተደራሽነትም አብዛኛውን የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚነት ያረጋገጡ መሆናቸውን ተናግሯል።
በዚሁ መሰረት የዘላቂ ልማት እቅዶችን ለማሳካት በሁለንተናዊ ድጋፍና ትብብር ከመደመር መንግስት ጎን በመሆን እኔም የድርሻዬን ለመወጣት ተዘጋጅቻለሁ ብሏል፡፡
የነገሌ ቦረና ከተማ ነዋሪ ወጣት አብዱባ ቦሩ፤ አብሮነት በዘላቂ ሰላምና ልማት የወጣቱን እድል ፈንታ የሚወስን እንደሆነ ገልጿል፡፡
የባህር በር ማግኘት የሀገርን ሉአላዊነትና ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር፣ እንዲሁም የዜጎችን ማህበራዊ ህይወት ለማሻሻል እጅግ ወሳኝ በመሆኑ ድጋፌን እገልጻለሁ ብሏል።
በሀገር ውስጥ ሰርቶ በመለወጥ ሰላም፣ ልማትና ብልጽግናን ማረጋገጥ ዘወትር የወጣቱ ዋና ፍላጎትና ተስፋ መሆኑን አንስቶ፤ የመደመር መንግስት የያዛቸው የአምስት ዓመታት የልማት ዕቅዶች እንዲሳኩም የወጣቶች ንቁ ተሳትፎና ድርሻ እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
በመደመር መንግስት ለወጣቶች በሀገር ውስጥ የተመቻቸው የሥራ ዕድል፣ የማምረቻ ቦታ እና የብድር አገልግሎትም ወደ ሥራ ለመሰማራት ትልቅ ማበረታቻና ተነሳሽነት እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል።