ቀጥታ፡

በክልሉ ከመደበኛ በላይ የሚጠበቀውን ዝናብ ለግብርና ምርታማነት ለማዋልና አደጋዎችን ቀድሞ ለመከላከል ዝግጅት ተደርጓል

ወላይታ ሶዶ፤ ጥቅምት 6/2019 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በቀጣይ ቀናት የሚጠበቀውን ከመደበኛ በላይ ዝናብ ለግብርና ምርታማነት ለማዋልና አደጋዎችን ቀድሞ ለመከላከል ዝግጅት መደረጉን የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።

የአገልግሎቱ ኃላፊ አቶ ኃይለማርያም ተስፋዬ፤ በክልሉ በቀጣይ ቀናት የሚጠበቀውን ከመደበኛ በላይ ዝናብና ሊደረግ የሚገባውን ቅድመ ጥንቃቄ አስመልክተው ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።

በኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት እና የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) ባወጡት የአየር ትንበያ መሠረት በቀጣዮቹ ወራት በክልሉ አብዛኛዎቹ አካባቢዎች ከመደበኛ በላይ ዝናብ ይጥላል ተብሎ ይጠበቃል።

በመሆኑም ዝናቡን ለግብርና ምርታማነት በአግባቡ ለመጠቀምና ሊከሰቱ የሚችሉ የተፈጥሮ አደጋዎችን በቅድሚያ ለመከላከል የሚያስችሉ ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችንና ተግባራትን መለየት መቻሉን አቶ ኃይለማርያም አስታውቀዋል።

በዚህም ዝናቡን ወደ ምርታማነት፣ ስጋቱን ደግሞ ወደ ዝግጁነት በመቀየር ለልማት የተፈጠረውን ዕድል በአግባቡ መጠቀምና ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎችን በቅድሚያ የመከላከል ተግባር ትኩረት እንደተሰጠው አንስተዋል።

በክልሉ የመኸር አምራች አካባቢዎች በዝናብ እጥረት ምክንያት የተስተጓጎሉ የግብርና ሥራዎችን ለማካካስ የሚጠበቀውን ዝናብ በአግባቡ መጠቀም ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም በኮንሶ፣ ኮሬ፣ ጋርዱላ እና ቡርጂ ዞኖች እና በሌሎችም አካባቢዎች የሚገኙ አርሶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች ከዝናቡ የበለጠ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የተቀናጀ ጥረት ሊያደርጉ እንደሚገባ አመልክተዋል።

ለዚህም በየደረጃው የሚገኙ የግብርና ተቋማት፣ አመራሮችና ባለሙያዎች አስፈላጊውን የግብርና ግብዓት፣ የቴክኒክ ድጋፍና የባለሙያ እገዛ በወቅቱ በማቅረብ የእርሻ ዝግጅቱን እንዲያፋጥኑ አስገንዝበዋል።

ከመደበኛው በላይ የሚጠበቀው ዝናብ ለመሬት መንሸራተት፣ ለጎርፍና ለሌሎች ተያያዥ አደጋዎች መንስኤ ሊሆን ስለሚችል ተጋላጭ በሆኑ በጋሞ፣ ጎፋ፣ ወላይታ፣ ጌዴኦ እና አሪ ዞኖችና መሰል አካባቢዎች ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በቆላማ እና አርብቶ አደር አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች ደግሞ ጎርፍና ሌሎች አደጋዎች ተከሰተው እንዳይጎዷቸው ቦዮችን የመቅደድና ማፋሰስ፣ በተጨማሪም ዝናቡን ለመኖ ልማትና የእንስሳት ሀብት ልማት እንደ ዕድል መጠቀም አለባቸው ብለዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ በደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች እና አካባቢው የሚኖሩ ዜጎች የኦሞ ወንዝ ውሃ ሞልቶ ከቱርካና ሐይቅ ከሚፈሰው ጎርፍ በመፍጠር ጉዳት እንዳያደርስ ማህበረሰቡ የወንዙን ሙላት በጥንቃቄ ሊከታተል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች የተጀመሩ የአደጋ መከላከል ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን ጠቅሰው፤ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓትን በመዘርጋት ችግሩን አስቀድሞ ለመከላከል እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

ከአየር መዛባት ጋር ተያይዘው ሊፈጠሩ የሚችሉ የአንበጣ፣ የግሪሳ ወፍና የውሃ ወለድ በሽታዎችም ሕዝቡ ላይ ያልተጠበቀ ጉዳት እንዳያደርሱ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የመከላከል ስራ ትኩረት ተደርጎ ወደ ተግባር መገባቱን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ለአደጋ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የሚኖሩ የክልሉ ነዋሪዎች የሚሰጡ የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃዎችን በትኩረት በመከታተል አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉም አሳስበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም