የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ መንገድን የተከተለ፣ ቀጣናዊ ምህዳሩንም ያገናዘበ ነው - ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ መንገድን የተከተለ፣ ቀጣናዊ ምህዳሩንም ያገናዘበ ነው - ምሁራን
ድሬዳዋ ፣ ጥቅምት 6/2018(ኢዜአ) የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ መንገድን የተከተለ ከመሆኑም ባሻገር ቀጣናዊ ምህዳሩን ከግምት ያስገባ ነው ሲሉ በድሬደዋ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ምሁራን ተናገሩ።
የባህር በር ጉዳይ ለኢትዮጵያ የፖለቲካ አጀንዳ ሳይሆን የህልውናዋና የኢኮኖሚ ዕድገቷ ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መግለጻቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ በጦርነት ሳይሆን በሰላማዊ፣ በንግድ ሕጎች እና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ብቻ ምላሽ እንዲያገኝ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አጽንኦት መስጠታቸውም እንዲሁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አያይዘውም የኢትዮጵያ የሁልጊዜም ፍላጎት ከጎረቤቶቿ ጋር በጋራ ማደግና መልማት መሆኑን አመልክተው የጎረቤት ሀገራት የኢትዮጵያን የባህር በር ጥያቄ ከልማትና ከትብብር ፍላጎት የመነጨ በመሆኑ በቀናነት እንዲረዱት ጥሪ ማቅረባቸውን ማስታወስ ይቻላል።
በድሬዳዋ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ምሁራንም የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ መንገድን የተከተለ ከመሆኑም ባሻገር ቀጣናዊ ምህዳሩን ከግምት ያስገባ መሆኑን ገልጸዋል።
በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር ተንሳይ ኃይሉ እንደገለጹት፤ የባህር በር ባለቤትነት ጉዳይ የትውልድ ሁሉ የጋራ አገራዊ ጥያቄና አጀንዳ ነው።
መንግሥት ይህንን አገራዊ ጥያቄ በሰላማዊ፣ ቀጠናዊ የጋራ ትብብርና ተጠቃሚነት ላይ በተመሰረተና በፍትሃዊ መንገድ ለማግኘትና ለመጠቀም እየሰራቸው የሚገኙት ተግባራት አበረታች ናቸው ብለዋል።
ያለ አግባብ የተነፈገውን ህጋዊ የባህር በር ባለቤትነት መብት መንግስት በዲፕሎማሲያዊ እና በሰጥቶ መቀበል መርህ የጀመረው ጥረት በትውልዱ እና በምሁራን ዘንድ ከፍተኛ መነቃቃት መፍጠሩን ረዳት ፕሮፌሰር ተንሳይ አስታውቀዋል።
ይህን ጥረት ለማሳካት ምሁራን በዕውቀት ላይ የተመሠረተ እገዛን በማጠናከር የኢትዮጵያን ህጋዊና ታሪካዊ መብት ለማረጋገጥ የድርሻቸውን ኃላፊነት ማጠናከር እንደሚገባቸውም አመልክተዋል።
በሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ የድሬዳዋ ካምፓስ ኃላፊ እና መምህር ሰለሞን ሰቦቃ በበኩላቸው፣ አገራችን ባልተገባ እና ምንም ማስረጃ በሌለበት ሁኔታ ከባህር በር መገለሏ ለከፍተኛ ማህበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ችግሮች መዳረጓን አንስተዋል።
መንግስት ዓለም አቀፍ ሕግን መሠረት በማድረግ እየከወነው ያለው ሰላማዊና ህጋዊ መንገድ የተከተለ አካሄድ የትውልዱ ጥያቄ የሆነውን የባህር በር የማግኘት መብት ሊያረጋግጥ እንደሚችል ሙሉ እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።
አገራችን የውኃና የኃይል ሀብቶቿን ለጎረቤት አገራት በማካፈል የሰጥቶ መቀበል መርህን በተግባር በማረጋገጥ በቀጣናው በጋራ ዕድገትና ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ እየሰራች መሆኑን አስታውሰዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ህጋዊ ጥያቄ ምላሽ ማግኘት ለቀይ ባህር እና ለአፍሪካ ቀንድ አገራት ዘላቂ ሰላም፣ ዕድገትና የጋራ ተጠቃሚነት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለውም አክለዋል።