ቀጥታ፡

በክልሉ ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ -ርዕሰ መስተዳድር የትምጌታ አስራት (ዶ/ር)

ሆሳዕና፤ ጥቅምት 6/2019 (ኢዜአ) ፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የትምጌታ አስራት (ዶ/ር) ገለፁ።

"በመደመር መንግስት፣ የህዝብ ድምፅ፣ የጋራ ተሳትፎ፣ የጋራ ልማት!" በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ የህዝብ ውይይት መድረክ በሆሳዕና ከተማ እየተካሄደ ነው።


 

ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንደገለጹት ከማህበረሰቡ ለሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ በመስጠት ተጠቃሚነቱ ይበልጥ እንዲረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቷል።

የመደመር መንግስት ህብረ ብሄራዊ አንድነትን አስጠብቆ ማስቀጠልንና ሁለንተናዊ ብልፅግናን ማረጋገጥን ያለመ የመደመር ስትራቴጂ አዘጋጅቶ ወደ ተግባር መግባቱን ተናግረዋል።

የአከባቢውን ፀጋዎችን ለይቶ በአግባቡ በመጠቀም የህዝቡ የጋራ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ የክልሉ መንግስት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ ስለመሆኑም ጠቁመዋል።

ህዝቡም ለዘላቂ ሰላም መጠበቅና ልማት መጠናከር ያለውን የላቀ ቁርጠኝነት ደምሮ በክልሉ የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ተሳትፎውን አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳድሩ አስገንዝበዋል።

ከህዝብ ለሚነሱ የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ከሚመለከታቸው አካላትጋር  በቅንጅት እንደሚሰራ ጠቅሰው የውይይት መድረኩ ዓላማ ቅንጅቱን በማጠናከር ልማትን ማፋጠን ነው ብለዋል።


 

የሀዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዮሀንስ አበጋ በበኩላቸው የመደመር መንግስት በየአካባቢው ያሉ ፀጋዎችን ለይቶ በማልማት የማህበረቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችል መርህ ተከትሎ እየተገበረ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ዞኑ በግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እንዲሁም ለቱሪዝም ዘርፍ እምቅ አቅም እንዳለው ጠቁመው በሁሉም ዘርፍ ያሉትን ፀጋዎች በመለየት የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በቅንጅት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

በመድረኩ በብልፅግና ፓርቲ የክልሉ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ሀላፊ ዲላሞ ኦቶሬ (ዶ/ር)ን ጨሞሮ ሌሎች የስራ ሃላፊዎችና  የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች እየተሳተፉ ነው ።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም