ቀጥታ፡

በሐረሪ ክልል የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለሚያረጋግጡ የኮሪደር እና የመሰረተ ልማት ሥራዎች ትኩረት ተሰጥቷል

ሐረር፤ ጥቅምት 6/2019 (ኢዜአ)፡-በሐረሪ ክልል የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለሚያረጋግጡ የኮሪደር እና የመሰረተ ልማት ሥራዎች ትኩረት መሰጠቱን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ከተማና ኮንስትራክሽን ቢሮ ሃላፊ ሙክታር ሳሊህ ገለጹ።

የመደመር መንግስት የተሻለ ሀገርን ለመገንባት የአሰራርና የአስተሳሰብ ማነቆዎችን በመፍታት በጋራ መልማት ላይ ይበልጥ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው።

በተለይ ከተሞችን የብልጽግና ማሳያዎች ለማድረግ ህብረተሰቡን ያሳተፉ ልማቶችን በፍጥነትና በጥራት በማከናወን ለስራ እድል ፈጠራና ለኑሮ ምቹ ማድረግ ላይ ቅንጅታዊ ተግባራት ቀጥለዋል።

በሐረር ከተማም ይህን መርህ በመከተል የኮሪደር እና ሌሎች የመሰረተ ልማት ሥራዎችን በማከናወን ከተማዋን ማራኪና ለኢንቨስትመንት  ተመራጭ  እንድትሆን  ማድረግ ተችሏል። 

በሐረሪ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ከተማና ኮንስትራክሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ ሙክታር ሳሊህ የመደመር መንግስት የህዝብን  የልማት ጥያቄዎች በተደራጀ መንገድ ለመፍታት ለቅንጅታዊ ሥራዎች ትኩረት መስጠቱን አንስተዋል። 

በተለይ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ሰው ተኮር የኮሪደር እና የመሰረተ ልማት ሥራዎችን እያከናወነ ነው ብለዋል።

በበጀት ዓመቱም ማህበረሰቡንና ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ የ18 ኪሎ ሜትር መንገዶች ግንባታ እና የመልሶ ማልማት  ሥራዎች  እየተከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የኮሪደርና ሌሎች የልማት ሥራዎች የሐረር ከተማን ጥንታዊነት በጠበቀ መልኩ እንደሚከናወኑ ገልጸው፣ በዚህም የከተማዋን ገጽታ ከማጉላት ባለፈ የህዝብን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

ለአብነትም በከተማው ቀበሌ 14 በተለምዶ "ቦቴ" በሚባለው አካባቢ የ17 ሄክታር መሬት መልሶ የማልማት ሥራ  መጀመሩን  በማሳያነት አንስተዋል።

የጀጎል ዓለም አቀፍ ቅርስ እድሳትና የኮሪደር ልማት እንዲሁም የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ግንባታን ከማከናወን ባለፈ በጀጎል ግንብ ውስጥ አራት ሄክታር መሬት መልሶ የማልማት ሥራ እየተከናወነ  መሆኑን ተናግረዋል።

የመኖሪያ ቤትና የንግድ ተቋማት ግንባታ እንዲሁም የአገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን የህብረተሰቡን እርካታ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑንም አቶ ሙክታር ጠቁመዋል።

ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥን ተደራሽ ለማድረግ በቴክኖሎጂ እና በሰው ሀይል አስፈላጊው የዝግጅት ሥራ መጠናቀቁም ተናግረዋል።

ለክልሉ ልማት የሚያስፈልገውን በጀት በራስ አቅም ለመሸፈን የገቢ አሰባሰብ ስርአቱን የማዘመንና ከብልሹ አሰራር ለመጠበቅ  እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም