ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ግብርና የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ በሚያስችል ትክክለኛ የምርትና ምርታማነት መስመር እየተጓዘ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 6/2019 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ግብርና የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ በሚያስችል ትክክለኛ የምርትና ምርታማነት መስመር እየተጓዘ መሆኑን የግብርና ምርምር ኢንስትቲዩት የሥራ ኃላፊዎች ገለጹ።

ትልቅ ሀገር፤ ትልቅ ሕዝብ፤ ታላቅ ርዕይ

ኢትዮጵያ በግብርና ዘርፍ ያላትን ሰፊ የተፈጥሮ ሀብትና አቅም ወደ ምርት በመቀየር የምግብ ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ ስትራቴጂክ የትኩረት መስክ በመቅረጽ አበረታች ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል።

የመደመር መንግሥት የግብርና ዘርፍ እመርታም በበጋ መስኖ ስንዴ፣ በሁሉም ወቅቶች የሰብል ምርት፣ የሌማት ትሩፋትና አረንጓዴ ዐሻራን በማሰናሰል የምግብ ሉዓላዊነትን የሚያረጋግጥ አቅም እየፈጠረ ነው።

በተለይም የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የሜካናይዜሽን እርሻ ሥርዓትን በማጎልበት የኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ከማጠናከር ባሻገር ለውጭ ገበያ ጭምር ማቅረብ ያስቻለ አበረታች ውጤት አስገኝቷል።

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብርም የአካባቢ ጥበቃና የሥነ-ምኅዳር ደኅንነትን በማስጠበቅ ለግብርና ለሁሉም የግብርና መስኮች የምርት ዘላቂነትን በማስጠበቅ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።

ይህም የመደመር መንግሥት የሚከተለው የብዝኅ ኢኮኖሚ ልማት ግብርናን ከባህላዊ አሠራር ወደ ዘመናዊ የምርት ምኅዳር በማሸጋገር የምግብ ዋስትናን የሚያረጋግጥ ምኅዳር መፍጠሩን ያመላክታል።

የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የሥራ ኃላፊዎች ለኢዜአ እንዳሉት፤ የመደመር መንግሥት የብዝኅ ኢኮኖሚ ልማትም ግብርናን ከአንድ ወቅት የምርት ጥገኝነት እንዲላቀቅ አድርጓል።

የኢትዮጵያን ግብርናም በጥናትና ምርምር በማስደገፍ ምርታማነትን የሚያሻሽሉ ምርጥ ዘሮችን በማፍለቅ ለአርሶና አርብቶ አደሩ ማኅበረሰብ ተደራሽ እያደረጉ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አማኑኤል ዓለሙ፤ ኢትዮጵያ የግብርና ምርታማነትን የሚያሻሽል ምቹ ሥነ-ምኅዳር የታደለች ሀገር መሆኗን አንስተዋል።

የመደመር መንግሥት ግብርናን ከአምስቱ የኢኮኖሚ አምዶች ጋር በማጣመር ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት ምርታማነትን በማሻሻል የምግብ ሉዓላዊነትን የሚያረጋግጥ አቅም እንዲፈጠር እያደረገ ነው ብለዋል።

ይህም ዘመናዊ የኩታ ገጠም ሜካናይዜሽን የእርሻ ሥርዓት በማጎልበት በስንዴና በሌሎች የሰብል ዓይነቶች ምርታማነትን በማሳደግ ለውጭ ገበያ ጭምር የሚተርፍ አቅም እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አብዮት መብራቴ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የግብርና ልማት የኢትዮጵያ የዕድገት መሠረት መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም የግብርና ምርታማነትን ለማላቅ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሽግግር የተመሠረቱ ውጤታማ የምርምር ሥራዎችን በማፍለቅ ለአርሶና አርብቶ አደሩ ተደራሽ እያደረጉ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ንጉሴ ደቻሳ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ በሚያስችል ትክክለኛ መስመር እየተጓዘች ነው።


 

ይህም የመደመር መንግሥት ለአርሶና አርብቶ አደሩ ምርጥ ዘርና የአፈር ማዳበሪያ ግብዓትን ጨምሮ ዘመናዊ የእርሻ መሣሪያ ተጠቃሚነትን ለማሻሻል ባደረገው ሰፊ ጥረት የመጣ መሆኑን ገልጸዋል።

የበጋ መስኖ ስንዴን ጨምሮ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የተሻሻለው የቡና ምርታማነትም የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ዓለም አቀፍ የገበያ ተወዳዳሪነት አቅምን እያጎለበተ መሆኑን ተናግረዋል።

በጥናትና ምርምር የተሻሻሉ የሰብልና የእንስሳት ዝርያዎችን በማፍለቅ ለአርሶና አርብቶ አደሮች ተደራሽ በማድረግ በግብርና ምርታማነት አወንታዊ አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆኑን አንስተዋል።

በቀጣይም የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ የግብርና ምርታማነት በማላቅ የምግብ ሉዓላዊነትን ከማረጋገጥ ባሻገር የዓለም አቀፍ ንግድ ተወዳዳሪነትን ለማጎልበት በትኩረት መሥራት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም