ቀጥታ፡

በድሬዳዋ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ተደራሽነት በማሳደግ ብቁ ስፖርተኞች ለማፍራት የተጀመረው ሥራ ይጠናከራል

ድሬዳዋ፣ ጥቅምት 6/2019 (ኢዜአ)፡-በድሬዳዋ አስተዳደር የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ተደራሽነት በማሳደግ ብቁ ስፖርተኞች ለማፍራት የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የአስተዳደሩ ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን አስታወቀ።

የድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽነር ኻሊድ መሐመድ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ባለፉት አምስት ዓመታት የወጣቶችን የስፖርት ማዘውተሪያ እና የመጫወቻ ጥያቄዎች ለመፍታት ውጤታማ ሥራዎች ተከናውነዋል።


 

በዚህም በየወረዳዎቹ ሰው ሰራሽ ሣር የተነጠፈላቸው ዘመናዊ የእግር ኳስ ሜዳዎችን ተገንብተው ጤናማነትና ብቁ ስፖርተኞችን ለማፍራት ሲሰራ መቆየቱንና ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

ለታዳጊዎች እና ወጣት ስፖርተኞች በክረምትና በበጋ ወራት የተለያዩ ስፖርታዊ ውድድሮችን በማዘጋጀት አቅማቸውን አውጥተው እንዲያሳዩና ተተኪነታቸውን በተግባር እንዲያረጋግጡ መደረጉንም ተናግረዋል።

በየወረዳው ከተገነቡት የእግር ኳስ ሜዳዎች ባሻገር ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ሁሉንአቀፍ ዘመናዊ የወጣቶች ስፖርት አካዳሚ መገንባቱንና በጥቂት ወራት ውስጥ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምርም አስታውቀዋል።

እንደ ኮሚሽነር ካሊድ ገለጻ፣ አካዳሚው ሁሉንም የስፖርት አይነቶች ማከናወን በሚያስችል መልኩ የተገነባ ነው።

በተጨማሪም የድሬዳዋ ስታዲየም አህጉራዊ ጨዋታዎችን ጭምር ማስተናገድ እንዲችል ከፍተኛ በጀት ተመድቦ የማስፋፊያ ሥራዎች እንደተከናወኑለት ኮሚሽነሩ ገልፀዋል።

ስታዲየሙ ደረጃውን ጠብቆ በአዲስ መልክ መገንባቱ ከድሬዳዋ ባሻገር ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋስትና እንዲሆን ማድረጉንም ጠቁመዋል።

 ስታዲየሙ የወንዶችና የሴቶች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአገራቸው በደጋፊያቸው ፊት እንዲጫወቱ ማስቻሉ ትልቅ እምርታ መሆኑን ጠቁመው፣ ይሄም በድሬዳዋ ስፖርተኞች ውስጥ ተስፋና መነቃቃት እየፈጠረ ይገኛል ብለዋል።

የድሬዳዋ የስፖርት ቤተሰቦች በበኩላቸው እንዳሉት አስተዳደሩ ለስፖርት ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት ተተኪ ስፖርተኞችን በብዛትና በጥራት ለማፍራት የሚያግዝ ነው።


 

ከስፖርት ቤተሰቦች መካከል አቶ አብዱልሰላም መሐመድ እና አቶ ቴዎድሮስ ኪዳኔ፤ ድሬዳዋ ስታዲየም በዘመናዊ መንገድ መገንባቱ በድሬዳዋ የሚካሄዱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎችን ለመመልከትና ለመደገፍ ያስችላል።


 

የስታዲየም ግንባታ ሥራው በሌሎችም ክልሎች ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸው፣ ይህም ኢትዮጵያ የ2028 የአፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት ያቀረበችው ጥያቄ ተገቢ ምላሽ እንዲያገኝ ያግዛል ብለዋል።


 

አስተዳደሩ ለስፖርት ዘርፍ የሰጠው ትኩረት የድሬዳዋን የቀድሞ የእግር ኳስ ዝና ለመመለስ ምቹ መደላድል እየፈጠረ መሆኑን የገለፀው ወጣት ኤልሻዳይ ደስታ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም