ኢትዮጵያ አህጉራዊ የእጅ ኳስ ውድድሮችን ታስተናግዳለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ አህጉራዊ የእጅ ኳስ ውድድሮችን ታስተናግዳለች
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 6/2019 (ኢዜአ) ፡-ኢትዮጵያ 34ኛው የአፍሪካ ታዳጊ ሴቶች እና 23ኛው የአፍሪካ ወጣት ሴቶች የእጅ ኳስ ውድድሮችን እንድታዘጋጅ ተመረጠች።
የኢትዮጵያን የአስተናጋጅነት ውሳኔ ያስተላለፈው የአፍሪካ እጅ ኳስ ኮንፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው።
ምክር ቤቱ በአንጎላ ሉዋንዳ ባካሄዳው መደበኛ ስብስባ በኢትዮጵያ እየታየ ያለው የእጅ ኳስ ስፖርት እድገት እና ውድድሮችን የማስተናገድ አቅም ለመመረጧ ምክንያት መሆኑን አመልክቷል።
በስብስባው ላይ የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን እና የምስራቅ አፍሪካ ዞን 5 ፕሬዝዳንት እንዲሁም የአፍሪካ እጅ ኳስ ኮንፌዴሬሽን ምክር ቤት አባል ፍትህ ወልደሰንበት (ዶ/ር) ተሳትፈዋል።
ፕሬዝዳንቱ ኢትዮጵያ ውድድሩን ለማዘጋጀት ዝግጁ መሆኗን አመልክተዋል።
በአፍሪካ የታዳጊ ሴቶች የእጅ ኳስ ውድድር ላይ 34 ሀገራት ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በወጣቶቹ ውድድር ላይ ከ15 በላይ ሀገራት እንደሚሳተፉ የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን መረጃ ያመለክታል።
አህጉራዊ ውድድሮቹ እ.አ.አ በ2027 ይካሄዳሉ።