የመደመር መንግሥት የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ስራዎችን እንደሚያጠናክር ጽኑ እምነት አለን - ኢዜአ አማርኛ
የመደመር መንግሥት የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ስራዎችን እንደሚያጠናክር ጽኑ እምነት አለን
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 6/2019 (ኢዜአ)፦ የመደመር መንግሥት የዜጎችን ሁለንተናዊ የላቀ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ስራዎችን እንደሚያጠናክር ባለፉት ዓመታት ያስመዘገባቸው ስኬቶች አመላካች ናቸው ሲሉ የሲቪክ ማህበራት ገለጹ።
የመደመር መንግሥት የወጣቶችና ስፖርት በሚኒስቴር ደረጃ በአዲስ መልክ መደራጀቱ ለወጣቶች ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት መጠናከር የተሰጠውን ትኩረት አመላካች መሆኑም ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ 7ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የምክር ቤቱ መመሥረቻ 1ኛ መደበኛ ስብሰባውን ማካሄዱ የሚታወስ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመደመር መንግሥት ካቢኔያቸውን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባጸደቁበት ወቅት የካቢኔ መረጣው ብቃትን፣ የሕዝብ አደራ መሸከምን፣ ሙስናን መጸየፍንና ስብጥርን ዋነኛ መስፈርት ተደርጓል ብለዋል።
የካቢኔ አባላት የተሰጣቸው ኃላፊነት ትልቅ በመሆኑ በትጋት መስራት እንደሚጠበቅባቸውና የሹመቱ ዋና ግብም ሕዝብን ማገልገልና የኢትዮጵያን መሻት፣ የሕዝብን ጥቅም ማዕከል አድርጎ መስራት መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አህመድ ሁሴን ለኢዜአ እንደገለጹት በምርጫ አሸንፎ መንግሥት መመስረት ማለት አደራ መቀበል፣ መሸከም፣ መወጣት እና በውጤታማነት መፈጸም ማለት ነው።
ከማህበረሰብ ጋር በቅርበት የመስራትና የማገልገል፣ ችግሮችን ተረድቶ ፈጣን ምላሽ መስጠት፣ ሰላም ማስፈን፣ ኢኮኖሚን ማሳደግ ማለት እንደሆነም ጨምረው ገልጸዋል።
የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሹመቱ መካተታቸው ለሀገር የሚጠቅሙ ጉዳዮች ላይ በትብብር መስራቱ የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል።
ከተሿሚዎችም በትብብር፣ በብቃት እና በታማኝነት ህዝብን ማገልገል እንደሚጠበቅ ጠቁመው ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ ለሀገሪቱ እድገት መስራት ይጠበቃል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶች ማህበር ፕሬዝዳንት እናትአለም እንዳለ በበኩላቸው በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በሀገሪቱ የዲሞክራሲ ስርዓት መጎልበቱንና ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ያመላከተ መሆኑን አንስተዋል።
በመንግስት ምስረታውም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የጾታና ሌሎች ስብጥሮች መካተታቸው ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ደረጃ ማሻገር የሚችል ምስረታ ተመልክተናል ብለዋል።
በካቢኔው በሀላፊነት የተካተቱ ሴቶችም በሀገር ሁለንተናዊ የልማት ጉዞ ላይ የራሳቸውን አሻራ በማበርከት ውጤታማ እንደሚሆኑ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በመንግስት ምስረታው ላይ የቀረቡ የትኩረት አቅጣጫዎች ለሀገሪቱ ፈጣን እድገት ያላቸውን ፋይዳ በመገንዘብ ከመንግስት ጎን በመቆም ለውጤታማነታቸው የበኩሉን ድርሻ ማበርከት እንደሚገባም ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ፕሬዝዳንት በረከት ብርብርሳ ቀደም ሲል በመደመር መንግሥት ለወጣቶች የተሰጠው ትኩረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያለውን ተስፋ ገልጿል።
በመንግሥት ምስረታው የወጣቶችና ስፖርት በሚኒስቴር ደረጃ በአዲስ መልክ እንዲደራጅ መደረጉ ለወጣቶች ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት መጠናከር የተሰጠውን ትኩረት ያመላክታል ብሏል።
በቀጣይም ወጣቶች በውሳኔ ሰጭነት፣ በልማትና በሌሎች ዘርፎች የሚኖራቸው አስተዋጽኦ የጎላ እንደሚሆን ይጠበቃል ሲል ተናግሯል።
ወጣቶችን በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ እና በማህበራዊ ዘርፎች የማብቃት ተግባራት ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ጠቁሟል።