ቀጥታ፡

በደሴ ከተማ የህብረተሰቡን የልማት፣ የሰላምና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ ትኩረት ተደርጓል

ደሴ ፣ጥቅምት 6/2019(ኢዜአ)፡- በደሴ ከተማ የህብረተሰቡን የልማት፣ የሰላምና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ ትኩረት መደረጉን የከተማው አስተዳደር ገለጸ።

የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዱባለ አብራሬ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ የመደመር መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የህብረተሰቡን የሰላም፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ በትኩረት ይሰራል።

ህብረተሰቡን በማሳተፍ የከተማዋን ሰላም በማስጠበቅ በቀጣይ አምስት ዓመታት ለሚካሄዱ የልማት ፕሮጀክቶች ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ወደ ተግባር መገባቱን ገልጸዋል።

በዚህም በሥራ እድል ፈጠራ፣ በሌማት ትሩፋት፣ በከተማ ግብርና፣ በገበያ ማረጋጋትና በሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ላይ በማተኮር እንደሚሰራ ተናግረዋል። 

ባለፉት ዓመታት የተገኙ አበረታች ውጤቶችን በማስቀጠል በትምህርት፣ በጤና፣ በመሰረተ ልማትና በሰው ተኮር ፕሮጀክቶች ላይ በማተኮር የከተማውን እድገት ለማፋጠን አቅጣጫ ተቀምጧል ብለዋል።

የአገልግሎት አሰጣጡን በቴክኖሎጂ በማዘመን የመልካም አስተዳደር ችግሮችንና ብልሹ አሰራሮችን በአንድ ማዕከል አገልግሎት ለመፍታት የተጀመረው ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ስርካለም አበበ በበኩላቸው፣ መንግስት ለህዝብ የገባውን ቃል ወደ ተግባር በመቀየር ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ በሚያደርገው ጥረት የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል። 


 

ባለፉት ዓመታት በኮሪደር ልማትና በሌሎች የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ረገድ የተሰሩ ስራዎች አበረታች ውጤት ማሳየታቸውን ጠቁመው በቀጣይ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል። 

ጅምር ስራዎችን በማስቀጠልና አዳዲስ ፕሮጀክቶችን በማስጀመር የከተማውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ በሚሰራው ስራ የድርሻቸውን እንደሚወጡም አረጋግጠዋል።


 

መንግስት በሥራ እድል ፈጠራ፣ በገበያ ማረጋጋት፣ በኮሪደር ልማትና የዲጂታል አሰራር ላይ የጀመራቸውን ስራዎች ማጠናከር እንዳለበት የተናገሩት  ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ተስፋነህ ነጋ ናቸው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም