ቀጥታ፡

‎በማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን አገልግሎት የተሟላ የህክምና አግኝተናል-በሀዋሳና አካባቢው ተጠቃሚዎች

ሀዋሳ፤ ጥቅምት 6/2019 (ኢዜአ)፡-የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን አገልግሎት አባል መሆናቸው ከፍለው ለመታከም የማይችሉትን የህክምና  አገልግሎት ጭምር ለማግኘት እንዳስቻላቸው በሀዋሳና አካባቢው ያሉ ተጠቃሚዎች ገለጹ፡፡

‎የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ በበኩሉ በበጀት ዓመቱ በማህበረሰብ አቅፍ ጤና መድኅን አገልግሎት ከ3 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የአባልነት ምዝገባና እድሳት ሥራ መጀመሩን አስታውቋል፡፡

በሀዋሳና አካባቢው የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የሆኑ ነዋሪዎች እንደገለጹት የጤና መድህን አባል በመሆናቸው በዓመት አንዴ በሚከፍሉት አነስተኛ ክፍያ ከአቅማቸው በላይ የሚጠይቁ የሕክምና አገልግሎቶችን ጭምር ለማግኘት አስችሏቸዋል፡፡

ከወንዶ ገነት ወረዳ ወደ ሀዋሳ አዳሬ አጠቃላይ ሆስፒታል ቤተሰብ ለማሳከምእንደመጡ የተናገሩት አቶ ሚልኪያስ ጋቹ በሆስፒታሉ ተገቢውን የሕክምና አገልግሎት ማግኘታቸውን ገልፀዋል፡፡

የጤና መድህን አገልግሎት አባል በመሆናቸው ያለምንም ተጨማሪ ወጪ ሙሉ የሕክምና አገልግሎት ማግኘታቸውን ገልፀዋል።


 

በሆስፒታሉ ወላጅ አባቷን እያሳከመች ያለቸው ወጣት ኢየሩሳሌም ብርሀኑ የጤና መድህን አገልግሎት አባል ባይሆኑ ኖሮ፣ ለአባቷ በተደረገላቸው ሕክምና ለከፍተኛ ወጪ ይዳረጉ እንደነበር ተናግራለች፡፡

በሆስፒታሉ በክፍያ ከሚታከሙ ተገልጋዮች እኩል የተሟላ የጤና ምርመራና የሕክምና አገልግሎት ማግኘት መቻላቸውን አክላ ገልፀለች፡፡

በአስም በሽታ ምክንያት በጠና ታመው ወደ ሆስፒታሉ እንደመጡ የተናገሩት ወይዘሮ ክብነሽ በዳሳ በበኩላቸው በተደረገላቸው የሕክምና ድጋፍ ጤናቸው እየተሻሻለ መምጣቱን ገልፀዋል፡፡


 

ለዓመታት የጤና መድህን ተጠቃሚ እንደሆኑ ገልጸው፣ መንግስት የጤና መድህን አገልግሎት ባይጀምር ኖሩ እሳቸውም ሆነ ባለቤታቸው የሕክምና ወጪውን ለመሸፈን ይከብዳቸው እንደነበር ተናግረዋል፡፡

የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ምክትልና የሕክምና አገልግሎት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሙንጣሻ ብርሀኑ በክልሉ ሁሉንም የህብተሰብ ክፍሎች  የአገልግለቱ ተጠቃሚ ለማድረግ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን አስታውሰው፣ በዚህም የተጠቃሚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል ብለዋል፡፡


 

ባለፈው ዓመት ከ2 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን የጤና መድህን አገልግሎት አባል መሆን ካለባቸው ዜጎች 85 በመቶውን መሸፈን መቻሉን ተናግረዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት ደግሞ ከ660 ሺህ በላይ ቤተሰቦችን ተደራሽ በማድረግ ከ 3 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ከመስከረም 20 ቀን 2019 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ወር የሚቆይ የምዝገባና የአባልነት እድሳት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል

ከዚህ ጎን ለጎን የጤና መድህን አገልግሎት ጥራትና ፍትሐዊነት ለማረጋገጥ ተቋማትን በምርመራ አገልግሎት ፣ በሰው ኃይል እና በመድኃኒት አቅርቦት የተሟሉ የማድረግ ሥራ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

ከዚህ በፊት በአገልግሎቱ ከፍተኛ ቅሬታ ይነሳበት የነበረውን የመድኃኒት አቅርቦት ችግር ለመፍታት በየመዋቅሩ ያሉ የአስተዳደር አካላት በጀት እንዲመድቡ ከማድረግ ባለፈ የህዝብ መድኃኒት ቤቶችን የማስፋፋት ሥራ መሰራቱን ጠቅሰዋል፡፡

በክልሉ ያሉ 28 የህዝብ መድኃኒት ቤቶችም ለጤና መድህን ተጠቃሚዎች አገልግሎት እንዲሰጡ ውል መገባቱንም አስታውቀዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም