የዳንጎቴ ነዳጅ ማጣሪያ አክሲዮን ሽያጭ በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የዳንጎቴ ነዳጅ ማጣሪያ አክሲዮን ሽያጭ በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ነው
አዲስ አበባ ፤ጥቅምት 6/2019(ኢዜአ)፦የዳንጎቴ ነዳጅ ማጣሪያ አክሲዮን ሽያጭ በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዳግማዊት ሽፈራው ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ከዳንጎቴ ኢንዱስትሪስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የዳንጎቴ ነዳጅ ማጣሪያ አክሲዮን ሽያጭ ማስተዋወቂያ መድረክ በአዲስ አበባ ተካሄዷል።
በመድረኩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ፣ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሽዴ፣ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዳግማዊት ሸፈራው፣ የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዮዲት ካሳ፣ የዳንጎቴ ግሩፕ መስራችና ዋና ሥራ አስፈፃሚ አሊኮ ዳንጎቴን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
የዳንጎቴ ነዳጅ ማጣሪያ አክሲዮን ሽያጭ ይፋ የተደረገው 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ካፒታል ለማሰባሰብ በማለም መሆኑም ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዳግማዊት ሽፈራው በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያን ለካፒታል ገበያ ምቹ ለማድረግ የሚያስችሉ ውጤታማ ሥራዎች ተከናውነዋል።
በዚህም ዘመናዊ ሥርዓት እየተዘረጋ መሆኑን ጠቁመው፣ የዳንጎቴ ነዳጅ ማጣሪያ አክሲዮን በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት መሆኑን ተናግረዋል።
ይህ ዕድል ለኢትዮጵያ ባለሀብቶች ትልቅ ዕድል ከመሆኑም በላይ በአፍሪካ ሀገራት መካከል ያለውን ትስስር ለማጠናከር ዓይነተኛ ሚና ይጫወታል ነው ያሉት።
አክሲዮኑ ብቁ ሆነው ለተገኙ ባለሀብቶች የሚሸጥ መሆኑንም አብራርተዋል።
የዳንጎቴ ግሩፕ መስራችና ዋና ሥራ አስፈፃሚ አሊኮ ዳንጎቴ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ በማዳበሪያ ምርት ፋብሪካ ለመገንባት መሠረት ጥለናል፤ በኢትዮጵያ እና በጅቡቲ መካከል የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር መዘርጋት የሚያስችል መሠረት ጥለናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ወደ ኢትዮጵያ የምናመጣውን ኢንቨስትመንት ማሳደግ እንፈልጋለን ያሉት አሊኮ ዳንጎቴ፣ የነዳጅ ማጣሪያው አክሲዮን ሽያጭ የዚሁ አካል ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ ባለው ተስማሚ የኢንቨስትመንት ከባቢ ኢንቨስትመንት እንድናጠናክር መሠረት ሆኖናል ሲሉም ገልጸዋል።