ቀጥታ፡

በክልሉ የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶችን በፍጥነትና በጥራት በማጠናቀቅ ለአገልገሎት ለማብቃት የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው

ወላይታ ሶዶ ፤ ጥቅምት 6/2019(ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶችን በፍጥነት በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ለማብቃት የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ መንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።

የክልሉ መንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ አቶ ኃይለማርያም ተስፋዬ፤ በክልሉ አዲሱ የመደመር መንግስት የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች የደረሱበትን የግንባታ ሁኔታ ተዘዋውሮ መመልከቱን ገልጸዋል።

የክልሉ ርእሰ መስተዳደር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) ጨመሮ ሌሎችም ከፍተኛ አመራሮች በግንባታ ላይ የሚገኙ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችን ከጎበኙ በኋላ ርእሰ መስተዳድሩ አቅጣጫ ማስቀመጣቸውን ተናግረዋል።

በግንባታ መዘግየት ምክንያት የሕዝብ ቅሬታ የፈጠሩ እንዳሉ በማንሳት እነዚህን ፕሮጀክቶች በተደመረ አቅም ሌት ከቀን በመስራት ማጠናቀቅ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ከተጀመሩ ፕሮጀክቶች መካከል የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ኮምፕሪሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የመልሶ ግንባታ ስራ፤ የወላይታ ሶዶ ከተማ ኮንክሪት አስፓልት መንገድ ግንባታ ስራ እና የወላይታ ሶዶ የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ስራ በተፋጠነ መልኩ ግንባታቸው እነዲጠናቀቁ ርእሰ መስተዳድሩ አቅጣጫ  አስቀምጠዋል ብለዋል።

የወላይታ ሶዶ ከተማ ኮሪደር እና ወንዝ ዳር ልማት ግንባታ በጥሩ ሁኔታ እየተሰራ መሆኑን አንስተው አጠናክሮ መቀጠል አንዳለበትም አንስተዋል።

በመሆኑም በክልሉ የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶችን በፍጥነትና በጥራት በማጠናቀቅ ለአገልገሎት ለማብቃት የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

የፕሮጀክቶች አፈፃፀም መለኪያው በተጨባጭ በተፈቱ የሕዝብ ጥያቄዎችና በመጡ ተጨባጭ ውጤቶች በመሆኑ አመራሩ ከህዝቡ ጋር በመተባበር ለልማት እቅዶች መትጋት እንደሚኖርበት አንስተዋል።

በግንባታ ላይ ያሉ እና በቀጣይም የሚሰሩ የልማት ፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው ጊዜ ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ በየደረጃው ያለው አመራር፣ ህዝቡ እና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም