የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 6/2019 (ኢዜአ) ፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሁለተኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ ሶስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ከቀኑ 9 ሰዓት ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከነገሌ አርሲ በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ በመጀመሪያ ጨዋታው በአዳማ ከተማ የ1 ለ 0 ሽንፈት አስተናግዷል።
ተጋጣሚው ነገሌ አርሲ ከቅዱስ ጊዮርጊስ አንድ አቻ ተለያይተዋል።
ሁለቱ ክለቦች በሊጉ የመጀመሪያ ድላቸውን ለማስመዝገብ ይጫወታሉ።
በሌላኛው መርሐ ግብር ሀላባ ከተማ ከባህር ዳር ከተማ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በሀላባ ኢንተርናሽናል ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
አዲስ አዳጊው ሀላባ ከተማ በመጀመሪያ የሊግ ጨዋታው ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ጋር አንድ አቻ ተለያይቷል።
ባህር ዳር ከተማ ሀዲያ ሀሳዕናን 1 ለ 0 ረትቷል።
ጨዋታው ሀላባ ከተማ የመጀመሪያ ሶስት ነጥቡን ለማግኘት፣ ባህር ዳር ከተማ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ የሚያደርጉት ነው።
ምሽት 12 ሰዓት ላይ ሸገር ከተማ ከአዳማ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዪኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።
በመጀመሪያ ሳምንት ሸገር ከተማ ኢትዮጵያ ቡናን፣ አዳማ ከተማ ኢትዮ ኤሌክትሪክን በተመሳሳይ 1 ለ 0 አሸንፈዋል።
ሁለቱ ክለቦች ተከታታይ ድላቸውን ለማስመዝገብ ይፋለማሉ።
ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከፋሲል ከነማ ሊያደርጉት ዛሬ ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ ወልዋሎ በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ከሊቢያው አል አህሊ ትሪፖሊ ጋር በሚያደርገው ጨዋታ ምክንያት ወደ ሌላ ጊዜ መተላለፉን የሊጉ አክሲዮን ማህበር አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት እስከ ጥቅምት 8 ቀን 2019 ዓ.ም ይቆያል።