ቀጥታ፡

የአውሮፓ ህብረት ለኢትዮጵያ ዘላቂ ልማት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋገጠ

አዲስ አበባ ፤ጥቅምት 6/2019(ኢዜአ)፦የአውሮፓ ህብረት ለኢትዮጵያ ዘላቂ ልማት የሚያደርገውን  ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጧል።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) የተመራ ልዑካን ቡድን በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) እና በዓለም ባንክ ዓመታዊ ስብሰባ ጎን ለጎን፣ ከአውሮፓ ህብረት የአለም አቀፍ ትብብር ኮሚሽነር ዮዜፍ ሲኬላ (Jozef Síkela) ጋር ተወያይቷል።

በዚህ ወቅት በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት ቅድሚያ በሚሰጣቸው የጋራ የልማት አጀንዳዎችና በቀጣይ ትብብሮች ዙሪያ መክረዋል።

የአውሮፓ ህብረት የአለም አቀፍ ትብብር ኮሚሽነር ዮዜፍ ሲኬላ (Jozef Síkela) በውይይቱ ወቅት ኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት አስተማማኝ አጋር መሆኗን ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ቀንድ እና በተለይም ለቀይ ባህር ቀጣና ሰላምና መረጋጋት የምታበረክተውን የላቀ አስተዋፅዎ እና በአፍሪካ ቀንድ ያላትን ስትራቴጂካዊ ቁልፍ ሚና አድንቀዋል።

አክለውም የአውሮፓ ህብረት ለኢትዮጵያ ዘላቂ የልማት ግቦች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም