ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ላይ የመገኘት እና የመጠቀም ሉዓላዊ መብት አላት-ግብጻዊው የፖለቲካ ተንታኝ ማግዲ ካሊሊ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 5/2019 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ላይ የመገኘት እና የመጠቀም ሉዓላዊ መብት እንዳላት ግብጻዊው የፖለቲካ ተንታኝ ማግዲ ካሊሊ ገለጹ።

ግብጻዊው ተንታኝ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ የሀገሪቷ አመራሮች ኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባህር ለመመለስ የምታደርገውን ጥረት በመቃወምና በማደናቀፍ ላይ የተመሠረተውን ፖሊሲያቸውን በጽኑ ተችተዋል።

ግብጽ አርቆ አሳቢና ብልህ መሪዎች ቢኖሯት ኖሮ፣ ኢትዮጵያ በቀይ ባህር እንድትጠቀም ከማደናቀፍ እና ከመቃወም ይልቅ ድጋፍ ያደርጉ ነበር ሲሉ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በቆዳ ስፋቷና በሕዝብ ብዛቷ ትልቅ የሆነች እና በየብስ የተከበበች ሀገር በመሆኗ፣ ወደ ቀይ ባህር የመድረስና የመጠቀም ሉዓላዊ መብት እንዳላት ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በታሪክ አጋጣሚ የባህር በር ባለቤት በነበረችበት ወቅት ቢሆን ለጎረቤት ሀገራት የስጋት ወይም የጉዳት ምንጭ ሆና እንደማታውቅ አስታውሰዋል።

በቀይ ባህር ዙሪያ የሚገኙ ሀገራት በጋራ ፍላጎቶቻቸው ላይ ተነጋግረው ቀጣናዊ መግባባት ለመፍጠር የሚያስችላቸው ውይይት እንዲያደርጉ ተንታኙ ጥሪ አቅርበዋል።

ጤናማ ያልሆነ ውድድርን አስወግዶ በትብብር መስራት ይገባል ያሉት ተንታኙ፣ሰላማዊ ስምምነቶች የኢትዮጵያን የባህር በር ፍላጎት በተግባር ለመመለስ መንገድ እንደሚከፍቱ ገልጸዋል።

አንዳንድ ሀገራት ለኢትዮጵያ የባህር በር የሚያስገኝ ስምምነት ለመፈራረም ዝግጁ ናቸው፤ የረጅም ጊዜ ውሎች ደግሞ በአፍሪካ ቀንድና በቀይ ባህር ቀጣና ዘላቂ ሰላምና ትብብርን ለማስፈን ጉልህ አስተዋፅኦ አለው ነው ያሉት።

ካይሮ በኤርትራ ጉዳይ የምትከተለውን የፖሊሲ አቅጣጫ የተቹ ሲሆን ግብፅና ሌሎች የዓረብ ሀገራት በ1960 እ.ኤ.አ ካይሮ ውስጥ ለተመሠረተው የኤርትራ ነፃነት ግንባር ያደርጉት የነበረውን ድጋፍ አውስተዋል።

እ.አ.አ በ1991 የኤርትራ ነፃ መውጣትና ኢትዮጵያ የባህር በር ማጣት፣ ለዚህ ውሳኔ መነሻ የሆኑ የቀጣናውን የፖሊሲ አቋሞች በድጋሚ መፈተሽ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።

ተንታኙ ግብፅ የኤርትራን የነፃነት ግንባር መደገፏ በሁለቱ ሀገራት መካከል ሊኖር የሚገባውን የወንድማማችነትና የትብብር ግንኙነት የጎዳ ታሪካዊ ስህተት እንደነበር አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም