ኢትዮጵያ በፋኦ “100 የልማት አርበኛ ሴቶች” መድረክ ዓለም አቀፍ ዕውቅና አገኘች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በፋኦ “100 የልማት አርበኛ ሴቶች” መድረክ ዓለም አቀፍ ዕውቅና አገኘች
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 5/2019 (ኢዜአ)፦የተባበሩት መንግሥታት የምግብና እርሻ ድርጅት (FAO) በግብርና እና ምግብ ሥርዓት እንዲሁም በገጠር ልማት ዘርፍ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ዕውቅና ለመስጠት ያዘጋጀው “FAO 100 Women Heroes” የተሰኘው ዓለም አቀፍ የዕውቅና መርሐ-ግብር በዛሬ ዕለት በጣሊያን ሮም በሚገኘው የድርጅቱ ዋና መሥሪያ ቤት ተካሂዷል።
በመርሐ-ግብሩም ኢትዮጵያዊቷ ወ/ሮ ሰናይት ገዛኸኝ በግብርና እና የምግብ ሥርዓትን በማጠናከር፣ የገጠር ልማትን በማሳደግ እና የማኅበረሰቡን የኑሮ ሁኔታ በማሻሻል ረገድ ላበረከቱት የላቀ አስተዋጽኦ ዕውቅና ማግኘታቸውን የግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል።
የዕውቅና ሽልማቱንም የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር Dr. Qu Dongyu ያበረከቱላቸው ሲሆን፣ ይህ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ኢትዮጵያውያን ሴቶች በግብርና እና ምግብ ሥርዓት፣ በገጠር ልማትና በማኅበረሰብ ለውጥ ላይ ያላቸውን ጉልህ ሚና የሚያሳይ መሆኑን ሚኒስቴሩ ገልጿል።
ይህ ስኬት ኢትዮጵያ በግብርና እና ምግብ ሥርዓት ዘርፍ ያላትን አዎንታዊ አስተዋጽኦ በዓለም አቀፍና በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ መድረኮች አጉልቶ ከማሳየቱም ባሻገር፣ ሀገራችን በግብርናው ዘርፍ ያላትን ልምድና ተሞክሮ ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ለማስተዋወቅ ጉልህ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብሏል።
ወ/ሮ ሰናይት ገዛኸኝ በጋምቤላ ክልል፣ መንገሽ ወረዳ፣ ኩሚ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ በየተለያዩ የግብርና ልማት ዘርፎች ማለትም የቡና ምርትን እና የእንስሳት እርባታ ኢንተርፕራይዞችን አቀናጅተው ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የግብርና ቢዝነስ በመገንባት ለማኅበረሰብ ለውጥ ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከቱ ያሉ ሞዴል የግብርና ሥራ ፈጣሪና የልማት አርበኛ ናቸው።