ተፈጥሮን የገራው የኮንሶዎች ታታሪነትና ጥበብ ማሳያ - ኢዜአ አማርኛ
ተፈጥሮን የገራው የኮንሶዎች ታታሪነትና ጥበብ ማሳያ
በሳሙኤል ወልደጊዮርጊስ (አዜአ-ሀዋሳ ቅርንጫፍ)
በርካታ ቱባ ባህሎች እና ባህላዊ የአስተዳደርና የዳኝነት ሥርዓት አለው፤ ተዝቆ የማያልቅ በተግባር የተፈተኑ የበርካታ አገር በቀል እውቀቶች ባለቤት መሆኑም ይነገርለታል የኮንሶ ማህበረሰብ።
ፈታኝ የሆነውን የአካባቢውን መልከዓ ምድር ጭምር በእርከን ሥራው ለእርሻ ሥራ ያዋሉትና በየዘመናቱ ተፈጥሮን ተንከባክቦ በትውልድ ቅብብሎሽ ዛሬ ድረስ ያቆየ የድንቅ ባህል ባለፀጋም ነው።
ወደኮንሶ ምድር ሲያቀኑ እንኳን ሜዳው ተራራው ጭምር በተካነች ባለሙያ ልቅም ተደርጎ የተሰራ ሽሩባ የሚመስለው የእርከን ስራቸው የብዙዎችን ቀልብ ይስባል።
የኮንሶ ማህበረሰብ በእርከን ሥራ፣ በአካባቢ ጥበቃ እና በጥንታዊ የእጅ መሣሪያዎቹ ይታወቃል። በተለይ በድንቅ የእርከን ጥበብ፤ የአፈርና ውሃ እቀባ ሥራ እና በጠንካራ የሥራ ባህል ተፈጥሮን ለሰው ልጅ ምቹ ያደረገ ማህበረሰብ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።
የኮንሶዎች የእርከን ጥበብ ለአፈር መሸርሸርና ለድርቅ የተጋለጠን አስቸጋሪን መሬት እንኳ በጠንካራ ስራቸው አፈሩን ከመሸርሸር መታደግ ብቻ ሳይሆን መልሶ ለግብርና ስራ በማዋል ጥቅም ላይ እንዲውል የሚያደርግ ነው።
የተራቆተው መሬት በእርከን ለምቶ ሲታይም አንዳች መስህብ ከመፍጠር ባለፈ ግርምትን ያጭራል። የኮንሶ የድንጋይ እርከኖች በዓይነታቸውም ሆነ በአሰራራቸው ውበትን የሚያላብሱና የአካባቢን መልክአ ምድር የሚጠብቁ ናቸው።
ተፈጥሮን መጠበቅና መንከባከብ ከኮንሶዎች የዕለት ተዕለት ሕይወት ጋር የተቆራኘ ተግባር ነው። ለእዚህም ጥሩ ማሳያ እንዲሆን ኮንሶዎች የአካባቢያቸውን መልክዓ-ምድር በባህላዊ የእርከን ሥራ በፈለጉት መንገድ ለመቀየርና ለመጠቀም የቻሉበት መንገድ መጥቀስ ይበቃል። ኮንሶዎች በዚህ ሥራቸው ዛሬም ድረስ ከሀገር ባለፈ ዓለምን ማስደመም ችለዋል።
ይህ ለዘመናት ከተፈጥሮ ጋር ያደረጉት ትግል አካባቢያቸውን በፈለጉት መንገድ እንዲጠቀሙ ከማድረግ ባለፈ አካባቢው ለበርካታ ቱሪስቶች መዳረሻ እንዲሆን አድርጓል። ይህም የኮንሶ ምድር የዓለም ቅርስ መገኛም ጭምር እንዲሆን አድርጓል።
የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጀት (ዩኔስኮ) የኮንሶዎች መገለጫ የሆነውን የእርከን ስራቸውን፣ የኑሮ ዘይቤያቸውንና ተፈጥሮን በሚፈልጉት መልኩ ለመጠቀም የሚያደርጉትን ትጋት መሰረት በማድረግ መልክዓ ምድሩን በዓለም የሰው ልጅ ወካይ ቅርስነት በመመዝገብ ዕውቅና ሰጥቶታል፡፡
የኮንሶ ማራኪ መልክዓ-ምድር በዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው ኤ.አ.አ. በ2011 ዓ.ም ሲሆን፤ መልክዓ ምድሩም በ23 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ነው፡፡ በውስጡም በባህላዊ መንገድ የተሰሩ እርከኖች፣ የካብ አጥሮች፣ የተከለሉ መንደሮችና ጎጆዎች ይዟል። ጥብቅ ደኖችም አሉት። መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ በተመልካች ላይ ግርምትን የሚጭሩ እነዚህ መንደሮች ከአራት መቶ ዓመት በላይ ዕድሜ ያስቆጠሩ ናቸው።
የኮንሶ ማህበረሰብ መለያና አሻራ የሆነው የእርከን ሥራም በኢትዮጵያ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ ከተማም መታየት ጀምሯል። በዚህም የእርከን ስራው ከኮንሶዎች ባለፈ ለሌሎች የሀገራችን አካባቢዎች በአርአያነት እየተወሰደ ነው ማለት ይቻላል። ለዚህም በአዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻ ልማት እና በእንጦጦ አካባቢው የተከናወነው የእርከን ሥራን መጥቀስ ይቻላል።
ኮንሶዎች የእርከን ሥራ መገለጫቸው እንዲሆን ያደረገው ዋናው ምስጢር ከትውልድ ወደትውልድ ሲተላለፍ የመጣው ታታሪነታቸው ነው። ጠንካራ የሥራ ባህል አላቸው፤ ከሌሎች ከመጠበቅ ይልቅ በራስ ሰርቶ ውጤታማ መሆን የኮንሶዎች መርህ ብቻ ሳይሆን የተገበሩት ጭምር መሆኑን አካባቢያቸውን መጎብኘት ብቻ በቂ ነው። የእነሱ ታታሪነት በራስ ጥረት ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ለተያዘው ሀገራዊ ግብም ጥሩ ግብአት ነው ማለት ይቻላል።
ኮንሶዎች በተፈጥሮ ፈታኝ የሆነውን መልከዓ ምድር በዚህ የእርከን ሥራቸው እጅ ሰጥቶ ለእርሻ ሥራ ያዋሉበት መንገድ አስደናቂና ለሌሎች አርአያም የሚሆን ነው። በዚህም ኮንሶዎች ተፈጥሮን በመንከባከብ በትውልድ ቅብብሎሽ ያቆዩ ድንቅ የባህል ባለፀጋዎች ናቸው ማለት ይቻላል።
ከሀገር ውስጥ የቱሪስት መዳረሻዎች መካከል አንዱ የሆነው ይሄው የኮንሶዎች መልክዓ ምድር ነው ለቱሪዝም ዘርፍ መጠናከርም አስተዋጾ እያደረገ ነው። በየዓመቱ በርካታ ቱሪስቶች አካባቢውን ይጎበኛሉ። በመልክዓ ምድሩ ያሉ የቱሪስት መስህቦች የብዙዎችን ቀልብ መሳብ ብቻ ሳይሆን ዛሬም የማህበረሰቡ የኑሮ ዘዬ ተጠብቆ ከትውልድ ትውልድ እየተላለፈ መምጣቱን ማሳያ ናቸው።
በዩኔስኮ የተመዘገብው ይህ መልክዓ ምድር የኮንሶዎች የዘመናት ድምር ውጤት ነው ማለት ይቻላል።በተለይ በንፋስ ተሸርሽሮ አሁን ያለውን የሕንጻ ቅርጽ እንደያዘ የሚነገርለትና ውብ የተፈጥሮ መስህብ በኮንሶ ተጠቃሽ የቱሪዝም መስህብ ነው። አካባቢው በኮንሶዎች አጠራር ጤሃማ የሚባል ሲሆን በተለምዶ "ኒው ዮርክ" እየተባለ ይጠራል።
የኮንሶዎች የስልጣኔ ምልክት የሆነው የእርከን ሥራም ከአካባቢው የአየር ጸባይ ጋር እንዴት ተስማምቶ መኖር እንደሚቻል ትውልድ የሚማርበትም ነው።
እነዚህና በአካባቢው ያሉ መሰል የመስህብ ሀብቶችን ጠብቆ ማቆየት የእኛ የዛሬው ትውልድ ድርሻ ነው። በተለይ የኮንሶዎች ጠንካራ የሥራ ባህል፣ ጥበቦችና ተፈጥሮን በመንከባከብ ለትውልድ ለማቆየትና ለልማት ለማዋል ያላቸው የካበተ ልምድ በአርአያነት ልንወስደው የሚገባ ነው።
ኮንሶዎች በየዘመናቱ ባሳዩት ታታሪነት የተገኘን ውጤት ለማስቀጠል የኮንሶን ባህላዊ መልክአ ምድር ከጥፋት መጠበቅ፣ መንከባከበ እና ለትውልድ ማስተላለፍ የሁላችንንም ትኩረት የሚፈልግ ነው።