ቀጥታ፡

12ኛውን የጣና ፎረም በስኬት በማስተናገድ የባህር ዳርን ገጽታ ከፍ ለማድረግ ተዘጋጅተናል -ወጣቶች

ባህር ዳር ፤ ጥቅምት 5/ 2019;-  በባህር ዳር ከተማ በሚካሄደው የጣና ፎረም ጉባኤ ስኬታማ በሆነ መልኩ እንዲጠናቀቅ የድርሻቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን  የከተማዋ ወጣቶች ገለጹ።

በአፍሪካውያን ሰላም፣ ልማት፣ ብልጽግናና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የሚመክረው 12ኛው የጣና ፎረም ከጥቅምት 13 እስከ 15/2019 ዓ.ም በባህር ዳር ከተማ ይካሄዳል። 

የከተማዋ አስተዳደር፣ ነዋሪዎች እና ወጣቶች እንግዶችን በኢትዮጵያዊ መልካም መስተንግዶ ተቀብለው ለማስተናገድ በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን  እየገለጹ ነው።

ፎረሙን አስመልክቶ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጠው  ወጣት ጌታሁን ደሴ እንደገለጸው፤ የጣና ፎረም የአፍሪካ መሪዎችና ባለሙያዎች በሰላምና ልማት ላይ የሚመክሩበት ሲሆን  ለባህር ዳር ከተማም ትልቅ ዕድል ይዞ የሚመጣ ሁነት ነው። 

"ፎረሙ ከተማችን ታላላቅ ዓለም አቀፍ ሁነቶችን በብቃት ማስተናገድ የምትችልና ሰላማዊ መሆኗን የምናሳይበት በመሆኑ ስኬታማ በሆነ መልኩ እንዲጠናቀቅም በቂ ዝግጅት አድርገናል" ብሏል።

የከተማዋ ወጣቶችም  እንግዶች የአገራችን ባህል በሚያስተዋውቅና የሚገልጽ መስተንግዶ በማድረግ ቆይታቸው አይረሴ እንዲሆን እንሰራለን ብሏል። 

በተጨማሪም እንግዶች በነጻነት ተንቀሳቅሰው የከተማዋን የልማትና የቱሪዝም ሀብቶች በመጎብኘት መልካም ገጽታዋን እንዲረዱ ጥረት እንደሚያደረግም ነው ያብራራው።

ሌላው የከተማዋ ነዋሪ ወጣት ታደለ ስማቸው፤ አህጉራዊ የሆነ ጉባኤ በባህር ዳር መካሄዱ የከተማዋን አስተማማኝ ሰላምና የቱሪዝም መዳረሻነት ለአፍሪካውያን ለማስተዋወቅ ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር ተናግሯል።


 

 "እያንዳንዱ ዜጋ ከተማዋ አስተማማኝ ሰላም የሰፈነባት መሆኗን ለዓለም የሚያሳይበት መድረክ ነው" ያለው ወጣት ታደለ፤ የከተማዋ ወጣቶች ለሰላም ዘብ በመቆም ኃላፊነታችን ለመወጣት ተዘጋጅተናል ነው ያለው።

ወጣት ብርቱካን ያዜ በበኩሏ፤ "የባህር ዳር ወጣቶች እንግዳ በመቀበልና ሰላምን በማስከበር ረገድ በቂ ልምድ አካብተናል" ወደ ፊትም ይሕንኑ አጠናክረን እንቀጥላለን ስትል ተናግራለች። 


 

ለዚህም በቅርቡ በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም በኢትዮጵያና ሴኔጋል ብሄራዊ ቡድኖች መካከል የተካሄደው የእግር ኳስ ጨዋታ በስኬት መጠናቀቁን በምሳሌነት ጠቅሳለች።

ወጣቱ በፎረሙ ወቅትም  የከተማዋን ሰላምና መልካም ገጽታ የመገንባት ትልቅ ኃላፊነት እንዳለበት በመገንዘብ ለዚሁ መዘጋጀት እንደሚገባም ነው የምትናገረው።

12ኛው የጣና ፎረም “በአፍሪካ የሰላም መንገዶች፡ የኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነትና የጂኦፖለቲካ ለውጥ” በሚል መሪ ቃል በባህር ዳር ከተማ እንደሚካሄድ ይታወቃል።

  

  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም