ቀጥታ፡

የመደመር መንግሥት ፕሮጀክቶች በፍጥነት፣ በጥራትና በተያዘላቸው ጊዜ ማጠናቀቅ መርሁ ነው

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 5/2019 (ኢዜአ)፦የመደመር መንግሥት የሚያከናውናቸው  የልማት ፕሮጀክቶችን በፍጥነት፣ በጥራትና በተያዘላቸው ጊዜ ገደብ አጠናቆ ለአገልግሎት ማብቃት መርሁ መሆኑን የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ የአማራ ክልል ፕሬዝደንት ጽህፈት ቤት እና ቤተ-መንግሥት ግንባታን አስጀምረዋል፡፡


 

ፕሮጀክቱ የመደመር መንግሥትን የሥራ ከባቢን በመለወጥ ደረጃቸውን የጠበቁ ጠንካራ ተቋማትን የመገንባት ርዕይን ማዕከል ያደረገ መሆኑን ተጠቁሟል፡፡ 

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ ፕሮጀክቱ የክልሉን ሕዝብ ታሪክ፣ ባህል፣ እሴቶችና የማንነት መገለጫዎች የሚያንፀባርቅ ታሪካዊ አሻራ መሆኑን ገልጸዋል።

በባህር ዳር ከተማ የነበሩትን ታሪካዊ ቅርሶችና አሻራዎች የመጠበቅና የመንከባከብ ሥራዎች መከናወናቸውን ያስታወሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ አዲሱ የርዕሰ መስተዳድር ቢሮ ግንባታ ፕሮጀክት የዘመኑን ዕድገትና የአስተዳደር አገልግሎት አሰጣጥ የሚመጥን ሆኖ እንደሚገነባ አስረድተዋል።

በተለይም ፕሮጀክቱ ከጣና ሐይቅና ከዓባይ ወንዝ መነሻ ጋር በተጣጣመ መልኩ ተፈጥሯዊ ውበቱን ጠብቆ የሚገነባ መሆኑ ልዩ እንደሚያደርገው ጠቅሰዋል፡፡

የመደመር መንግሥት  ፕሮጀክቶች በፍጥነትና በጥራት መጠናቀቃቸው ጥብቅ መርህ መሆኑን በመጥቀስ፤ ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜና ጥራት እንዲጠናቀቅ ኮንትራክተሩ፣ አማካሪውና ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ጥረት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም