ቀጥታ፡

ማህበራዊ ሚዲያን ለሀገር ልማትና ለዜጎች አብሮነት በሚጠቅም መልኩ በኃላፊነት መጠቀም ይገባል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 5/2019 (ኢዜአ)፦ማህበራዊ ሚዲያን ለሀገር ልማት፣ ለዜጎች አብሮነትና አንድነት መጠናከረ በሚጠቅም መልኩ በኃላፊነት መጠቀም እንደሚገባ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ ፀጋ ገለጹ።

ኢንስቲትዩቱ "የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም እና አስፈላጊነት በኢትዮጵያ" በሚል ርዕስ ያካሄደውን አጠቃላይ ጥናት ይፋ አድርጓል።


 

ጥናቱን አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጡት አቶ ፍቃዱ ፀጋ፤ ዲጂታላይዜሽን ለሀገረ-መንግሥት ግንባታ አይነተኛ ሚና እንዳለው ገልጸዋል። 

ማህበራዊ ሚዲያን በአግባቡ መጠቀም የጋራ ትርክትን ለመገንባት፣ በክህሎትና በእውቀት የዳበረ ትውልድ ለመፍጠር እና ሀገራዊ እሳቤዎችን ለማስረፅ ከፍተኛ አዎንታዊ ሚና እንደሚጫወት አብራርተዋል።

ባለፉት ዓመታት ማህበራዊ ሚዲያ ለሀገረ-መንግሥት ግንባታ ጥቅም ላይ እንዲውል የተደረጉት ጥረቶች በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች የላቀ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ጠቅሰዋል።

የጥላቻ ንግግርን እና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣው አዋጅ ማህበራዊ ሚዲያን ለመምራትና በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል አስቻይ ሁኔታ መፍጠሩንም ጠቁመዋል፡፡ 

ማህበራዊ ሚዲያን በአግባቡ በመጠቀም ለሀገረ-መንግሥት ግንባታ፣ ለህዝቦች አብሮነት እና ለሁለንተናዊ እድገት የሚያበረክተውን አወንታዊ አስተዋጽኦ በላቀ ደረጃ ማሳካት ይቻላል ብለዋል፡፡ 

በመሆኑም ማህበራዊ ሚዲያን ለዜጎች አብሮነት በሚጠቅም መልኩ የመጠቀም ባህልን ማሳደግ እንዲሁም የዲጂታል ምህዳሩን ህግ እና ስነ-ምግባር አክብሮ የመንቀሳቀስ ሃላፊነትን ማጠናከር እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ትምህርት ቤት መምህርና ተመራማሪ አብዱላዚዝ ዲኖ (ዶ/ር) በጥናቱ ይዘት ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም በኢትዮጵያ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ጠቅሰው መድረኩን በእውቀት፣ በክህሎት እንዲሁም ሀገራዊ አንድነትና አብሮነትን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ከመጠቀም አኳያ ክፍተቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል።


 

በጥናቱ ማህበራዊ ሚዲያ ይዞ የመጣውን አዎንታዊ እድል ወደ ዘላቂ ጥቅም በመቀየር ረገድ አዎንታዊ ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑም መዳሰሱንም ጠቁመዋል፡፡

የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎችን የስነ-ምግባር እና የዲጂታል ክህሎት አቅም ይበልጥ ለማጎልበት፣ አወንታዊ አጠቃቀምን የሚያበረታቱ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብሮች በተለያዩ አማራጮች ሊዘጋጁ እንደሚገባ ጥናቱ አመላክቷል ብለዋል።

ጥናቱ ማህበራዊ ሚዲያን ተከትሎ በሀገርና በዜጎች ላይ የሚደርሱ አሉታዊ ተፅዕኖዎችን ለመከላከል ግልጽና ተፈጻሚ የሚሆኑ ህጎች ስራ ላይ ሊውሉ እንደሚገባ አሳስቧል። 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም