ቀጥታ፡

በክልሉ እየተደረገ ያለው የሰብአዊ ድጋፍ ለወቅታዊ ችግር ፈጣን ምላሽ መስጠት ያስቻለ ነው

ሰመራ፣ጥቅምት 5/2019 (ኢዜአ)፡- በአፋር ክልል በመንግስት እየተደረገ ያለው የሰብአዊ ድጋፍ ለወቅታዊ ችግር ፈጣን ምላሽ መስጠት ያስቻለ መሆኑን የድጋፉ ተጠቃሚዎች ተናገሩ።

የአፋር ክልል የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በበኩሉ በክልሉ የቅድሚያ ቅድሚያ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች የሰብአዊ ድጋፍ በአግባቡ እየተዳረሰ መሆኑን ገልጿል።

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ከአዳማ የእህል ማከማቻ ማእከላዊ መጋዘን ወደ አፋር ክልል በሁለት ዙር የሰብአዊ ድጋፍ መላኩ ይታወቃል።


 

በዚሁ መሰረትም የመጀመሪያው ዙር አፋር ክልል ደርሶ የቅድሚያ ቅድሚያ የሰብአዊ ድጋፍ ይሰጣቸዋል ተብለው ለተለዩ አካባቢዎች በመከፋፈል ላይ ይገኛል።

በድጋፉ ተጠቃሚ የሆኑ ወገኖችም በመንግስት እየተደረገ ያለው የሰብአዊ ድጋፍ ለወቅታዊ ችግር ፈጣን ምላሽ መስጠት ያስቻለ መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሉ ዱቢ ወረዳ የሚኖሩትና የድጋፉ ተጠቃሚ የሆኑት ወይዘሮ አሲያ መሐመድ፤ በአካባቢው በተከሰተው ድርቅ ለችግር የተጋለጡ መሆኑን አንስተው በመንግስት በተሰጠው ፈጣን ምላሽ መደሰታቸውን ተናግረዋል።

በመንግስት የተደረገው የሰብአዊ ድጋፍ ለወቅታዊ ችግር ፈጣን ምላሽ በመስጠት የአካባቢውን ነዋሪዎች ችግር ያቃለለ ስለመሆኑም ገልጸዋል።

በመሆኑም በመንግስት የተደረገላቸው ድጋፍ እርሳቸውና ቤተሰባቸው ላጋጠማቸው ችግር መፍትሄ መሆኑን ገልጸው ስለተደረገላቸው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።


 

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ መሐመድ አሀው፤ በፌዴራልና በክልሉ መንግስት እየተደረገ ያለው የሰብአዊ ድጋፍና እገዛ የብዙዎችን ችግር የሚያቃልል በመሆን ገልጸዋል።

በዝናብ እጥረት ምክንያት በአካባቢው ድርቅ በመከሰቱ ብዙዎች ችግር ላይ የወደቁበት ወቅታዊ ችግር ስለመፈጠሩ አንስተው ይህንን ሁኔታ በአግባቡ በመረዳት መንግስት ፈጣን ምላሽ መስጠቱን አድንቀዋል።

በመሆኑም በአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ስለተደረገልን ፈጣን የሰብአዊ ድጋፍ ምስጋናችንን እናቀርባለን ብለዋል።


 

የአፋር ክልል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የክምችት ጥራትና ቁጥጥሮ ቡድን መሪ አቶ መሐመድ አብደላ፤ የሰብአዊ ድጋፉ ተደራሽነት በተፋጠነ መልኩ ለሚመለከታቸው ወገኖች እየደረሰ መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ ቀደም ብሎ በተደረገው ልየታ የቅድሚያ ቅድሚያ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች የሰብአዊ ድጋፍ በአግባቡ እየተዳረሰ ይገኛል ብለዋል።

በአፋር ክልል በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ችግር ለገጠማቸው ወገኖች የሰብአዊ ድጋፍ ተደራሽ እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን መግለጹ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም