የተጣለብንን ኃላፊነት በተግባር በመተርጎም የህዝቡን ተጠቃሚነት በበለጠ ለማረጋገጥ እንተጋለን - ኢዜአ አማርኛ
የተጣለብንን ኃላፊነት በተግባር በመተርጎም የህዝቡን ተጠቃሚነት በበለጠ ለማረጋገጥ እንተጋለን
ወላይታ ሶዶ፤ ጥቅምት 5/2019 (ኤዜአ)፦ከመንግስትና ህዝብ የተሰጠንን ኃላፊነት በተግባር በመተርጎም የሕዝቡን ተጠቃሚነት በበለጠ ለማረጋገጥ ተግተን እንሰራለን ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የስራ ሃላፊዎች ተናገሩ።
በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ብልጽግና ፓርቲ አብላጫ ድምጽ ማግኘቱን ተከትሎ የመንግስት ምስረታ መካሄዱ ይታወቃል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ኢዜአ ያነጋገራቸው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የስራ ኃላፊዎች፤ የተሰጣቸውን የህዝብና የመንግስት ኃላፊነት በተግባር በመተርጎም ለህዝብ ተጠቃሚነት ተግተው እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡
የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ካርታ ካስኬ(ዶ/ር) በክልሉ የግብርና ትራንስፎርሜሽንን ለማሳካት በልዩ ትኩረት እንደሚሠራ ጠቁመዋል።
ያሉትን አቅሞች በመጠቀም ምርታማነትን ማሳደግ እንዲሁም በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ረገድ እመርታ ማሳየት፣ ግብርናን ማዘመንና የመስኖ ልማቱን ማስፋት ልዩ ትኩረት የተሰጣቸው ተግባራት መሆናቸውን አብራርተዋል።
በተለይም በቡና፣ በሰብልና በመኖ ልማት ላይ የሕዝቡን የበለጠ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጥረት ይደረጋል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም የሌማት ትሩፋትን ጨምሮ እየተተገበሩ ያሉ ኢኒሼቲቮችን ውጤታማነት በማጎልበት የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ተግባራት እንደሚጠናከሩ ገልጸዋል፡፡
በክልሉ ያለውን የጤና አገልግሎት ሥርዓት በማጠናከርና የአገልግሎት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ መገባቱን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳዊት ደሳለኝ ናቸው።
የመጀመሪያ ደረጃ የጤና አገልግሎት ሥርዓትን በማጠናከር በተለይም በጤና ኬላዎች፣ በጤና ጣቢያዎችና በመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች የሚሰጠውን የጤና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነት ለማሻሻል እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
የጤና ዘርፍ አመራሩና ባለሙያው የተጣለበትን ኃላፊነት ከተጠያቂነት ጋር አጣምሮ ማስኬድ እንዳለበት ያመለከቱት ኃላፊው የሕዝብን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ዋናው ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ መስፍን መንዛ (ዶ/ር) በበኩላቸው የትምህርት ጥራት ችግርን በመፍታት የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል በተለየ ትኩረት እንደሚሠራ ተናግረዋል።
በሚቀጥሉት ጊዜያትም ከሀገር አቀፍ የትምህርት ፍኖተ ካርታ የወጡ የትምህርት ልማት ሥራዎች ላይ ትኩረት እንደሚደረግ አመላክተዋል።
የመማር ማስተማር ሥራውን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግም የተማሪዎች ምገባን ማሳለጥ፣ የትምህርት ሥርዓቱን ማጠናከርና የትምህርት አመራሩን አቅም ማሳደግ ልዩ ትኩረት የሚሰጣቸው ተግብራት መሆናቸውን አመላክተዋል።
በትምህርት ጥራት ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተባብሮ በመስራት ለውጥ ለማምጣት በበለጠ ትጋት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።