ቀጥታ፡

በክልሉ የመንግስት አገልግሎትን በማዘመን ቀልጣፋና ፍትሐዊ አሰራርን የማስፈን ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል -ርዕሰ መስተዳድር ፍቅሬ አማን

ቦንጋ፤ ጥቅምት 5/2019 (ኢዜአ):-በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አሰራርን በማዘመን ለተገልጋይ ቀልጣፋና ፍትሐዊ አገልግሎት ለመስጠት የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ፍቅሬ አማን ገለፁ።

ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ፍቅሬ አማን የክልሉን መንግስት የቀጣይ የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የሰላም አቅጣጫዎችን አስመልክተው ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።

ርእስ መስተዳድሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት የመንግስት አገልግሎት በማዘመን ህብረተሰቡ ፈጣን፣ ቀልጣፋና ፍትሀዊ አገልግሎት እንዲያገኝ የተጀመረው ሥራ  ተጠናክሮ ይቀጥላል ። 

በአሁኑ ወቅትም የህብረተሰቡን የመልካም አስተዳደር ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት የህዝቡን ጊዜ፣ ሀብትና ጉልበት በሚቆጥብ መልኩ ዘመናዊ አገልግሎቶችን የማስፋት ሥራ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

በአገልግሎት አሰጣጥ ያልተገባ ጥቅምና ሀብት ለማካበት የሚፈጸሙ የሙስና ድርጊቶችን ለመከላከል ክትትሉን ከማጠናከር ባለፈ የህግ የበላይነትን የማስከበር ሥራ ይሰራል ብለዋል። 

ህብረተሰቡን በማስተባበር ሙስናና ብልሹ አሰራርን መታገል ካልተቻለ አገልግሎትን ከማዛባት ባለፈ በክልሉ ለማረጋገጥ  የተጀመረውን የብልፅግና ጉዞ ማሳካት እንደማይቻል አስረድተዋል።

በተለይ አመራሩ ከህዝብና ከመንግስት የተሰጠውን ሀላፊነት በቅንነትና በታማኝነት በመወጣት የሕዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ ጠንክሮ መስራት እንዳለበት አሳስበዋል።

በየተቋማቱ የሚሰጡ አገልግሎቶችን በማዘመንና ከእጅ ንክኪ የፀዳ በማድረግ ለብልሹ አሰራር በር የሚከፍቱ ሁኔታዎችን የመዝጋት ሥራ ይከናወናል ብለዋል።

መሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ብልሹ አሰራርና ሙስና የምንከላከልበት አንዱ መንገድ መሆኑን  የገለፁት አቶ ፍቅሬ፤ በክልሉ ስድስት ማዕከላት ተገንብተው ለአገልግሎት መብቃታቸውን ገልፀዋል።

በማዕከላቱ ፈጣን የመንግስት አገልግሎት መሰጠቱ በሕዝቡ ዘንድ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ  እንዲያገኙ ያግዛል ብለዋል። 

ማዕከላቱን በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ ከማስገባት ጎን ለጎን ተጨማሪ ማዕከላት በመገንባት ህብረተሰቡ ፈጣን፣ ቀልጣፋና ፍታሐዊ አገልግሎት እንዲያገኝ የተጀመረው ሥራ ይቀጥላል ብለዋል። 

ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት የሚሰሩ ህገወጥ ሥራዎች የሀገርን ጥቅም የሚጎዱና ልማትን የሚያደናቅፉ በመሆናቸው የክልሉ መንግስት የተጠናከረ እርምጃ ይወስዳል ብለዋል።

ይህም ውጤታማ እንዲሆን ህብረተሰቡ አገልግሎት ማግኘት መብቱ መሆኑን በአግባቡ ሊረዳ ይገባል ያሉት አቶ ፍቅሬ፣  ሙስናን በመከላከል ተግባርም የበኩሉን እንዲወጣ አሳስበዋል። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም