ቀጥታ፡

ሀብትን አውቆና አበልጽጎ ለትውልድ የሚተርፍ ወረት መፍጠር የመደመር መንግሥት ዋነኛ ዓላማ ነው - አቶ ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 5/2019 (ኢዜአ)፦የመደመር መንግሥት ዋና ዓላማ ያሉትን ሀብቶች አውቆና አበልጽጎ ለተከታዩ ትውልድ የሚተርፍ ወረት መፍጠር መሆኑን የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት የአማራ ክልል ፕሬዝደንት ጽህፈት ቤት እና ቤተ-መንግሥት ግንባታን ባስጀመሩበት ወቅት ነው።


 

ፕሮጀክቱ የመደመር መንግሥትን የሥራ ከባቢን በመለወጥ ደረጃቸውን የጠበቁ ጠንካራ ተቋማትን የመገንባት ርዕይን ማዕከል ያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግንባታ ማስጀመር ስነ-ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግርም፣ ፕሮጀክቱ የክልሉን ገጽታ የሚመጥን እንዲሁም የጣናንና የዓባይን ተፈጥሯዊ ውበት ባማከለ መልኩ የሚገነባ መሆኑን ገልጸዋል። 

ፕሮጀክቱ ከመደበኛ የመንግሥት ሥራዎች ማከናወኛነቱ ባለፈ፣ ተጨማሪ የኢኮኖሚና የቱሪዝም ሀብት መፍጠሪያ ሆኖ የሚያገለግል መሆኑን ጠቁመዋል። 


 

የመደመር መንግሥት ሀብትን በማልማት ለትውልድ የሚተርፍ ወረት ለመፍጠር እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷንና ዳር ድንበሯን ሙሉ በሙሉ የምታስከብር፣ የባህር በር ባለቤትነት መብቷን ለማረጋገጥና በሁሉም መስክ ለአፍሪካ ምሳሌ የምትሆን የበለጸገች ሀገር እንድትሆን እየተሰራ ይገኛል ሲሉ ገልጸዋል።

ባህር ዳር ከተማ በጥቂት ዓመታት ውስጥ በከፍተኛ ፍጥነት በማደግ ለነዋሪዎቿና ለጎብኚዎቿ ምቹና ውብ መሆኗን ገልጸዋል። 


 

ከተማዋን የበለጠ ለማሳመርና የቱሪዝም እምቅ አቅሟን ለማጎልበት ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የመንገደኞች አየር መንገድ ተርሚናል ተገንብቶ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ጠቁመዋል፡፡ 

በተጨማሪም ደረጃውን የጠበቀው ስታዲየም የሀገራችንን ብሔራዊ ቡድን ወደ ሀገሩ በመመለስ ለስፖርት ዘርፉ መነቃቃት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ጠቁመው የኮሪደር ልማት የከተማዋን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ማዘመኑን አንስተዋል።

በተጨማሪም እንደ ሀገር በቅርቡ ሥራ የጀመሩት የብሔራዊ ውድ ማዕድናት ማጣሪያ ፋብሪካ የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ አቅም በአዲስ መልክ ከፍ የሚያደርጉ ትልቅ ምዕራፍ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በቀጣይም የክልሉ ህዝብና አመራር ተቀናጅተው በመሥራት የክልሉን የልማት ስራዎች አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም