በአማራ ክልል የጡት ካንሰር በሽታን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ አበረታች ውጤት ተመዝግቧል - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል የጡት ካንሰር በሽታን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ አበረታች ውጤት ተመዝግቧል
ደሴ፣ጥቅምት 5/2019(ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል የጡት ካንሰር በሽታን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ የተጠናከረ ሥራ በመሠራቱ አበረታች ውጤት መመዝገቡን የክልሉ ጤና ቢሮ ገለጸ።
የክልሉ ጤና ቢሮ ከደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ጋር በመተባበር የጡት ካንሰር ግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በደሴ ከተማ አካሄዷል።
በቢሮው የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ኦፊሰርና የካንሰር ክፍል አስተባባሪ ዶክተር ቴዎድሮስ ጌታቸው እንደገለጹት፤ የጤና ፖሊሲው በሽታዎችን ቀድሞ በመከላከልና አክሞ በማዳን ላይ ያተኮረ ነው።
በዚህም ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለመቀነስ በቅድመ ምርመራና አክሞ በማዳን ሥራዎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተተገበረ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በተለይም በሴቶች ላይ ጉዳት እያደረሰ የሚገኘውን የጡት ካንሰር በሽታ በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ የተጠናከረ ሥራ በመሠራቱ አበረታች ውጤት ማመዝገብ መቻሉን ተናግረዋል።
የጡት ካንሰር ሕክምና በቴክኖሎጂ በመታገዝ ጥራት ባለው መንገድ እየተሰጠ መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር ቴዎድሮስ፤ እየተፈጠረ ያለው ተከታታይነት ያለው ግንዛቤ ሕብረተሰቡ ለምርመራና ለሕክምና ትኩረት እንዲሰጥ ማስቻሉን አስረድተዋል።
በተለይ በጥቅምት ወር በዘመቻ ጭምር ግንዛቤ እየተፈጠረ መሆኑን ጠቁመው፤ ሕብረተሰቡ በአቅራቢያው ወደሚገኝ ጤና ተቋም በመሄድ በነፃ መመርመር እንደሚችል ገልጸዋል።
የደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ሐይማኖት አየለ በበኩላቸው፤ ሆስፒታሉ የአገልግሎት አሰጣጡን በማዘመን ጥራት ያለው ሕክምና እየሰጠ ይገኛል ብለዋል።
በተለይ የጡት ካንሰር በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በዘመቻ ጭምር በነፃ ምርመራ በማካሄድ፣ ሕመምተኞች ፈጥነው ሕክምና እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በያዝነው ጥቅምት ወርም ምርመራው በነፃ መጀመሩን ጠቁመው፤ ሕብረተሰቡ ወደ ሆስፒታሉ በመሄድ መመርመርና መታከም የሚችልበት አሠራር መዘርጋቱን አስረድተዋል።
በወሎ ዩኒቨርሲቲ የጤና ትምህርት ክፍል መምህርና በሆስፒታሉ የካንሰር ስፔሻሊስት ሐኪም ዶክተር ያሲን ወርቁ በበኩላቸው፤ የጡት ካንሰር በሽታ በወቅቱ መታከም ከተቻለ በቀላሉ ማዳን የሚቻል መሆኑን ተናግረዋል። በመሆኑም ሕብረተሰቡ በወቅቱ መመርመር፣ መታየትና መታከም እንዳለበት መክረዋል።
"በወቅቱ መመርመርና መታከም በመቻሌ ከጡት ካንሰር በሽታ ነፃ መሆን ችያለሁ" ያሉት ደግሞ የደሴ ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ ሰርኬ ከበደ ናቸው።
የሕመም ስሜት ሳይሰማቸው ከጡታቸው ላይ እብጠት በማየታቸው ፈጥነው ወደ ጤና ተቋም በመሄድ ሲመረመሩ የጡት ካንሰር መሆኑን ማወቃቸውን የገለጹት ወይዘሮ ሰርኬ፤ ባደረጉት የሕክምና ክትትል ሙሉ በሙሉ መዳን በመቻላቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል።
በመድረኩ የክልል፣ የዞን፣ የሆስፒታል፣ የከተማና የወረዳ አመራሮች፣ ባለሙያዎችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።