የምክር ቤቱን የአሠራርና የአደረጃጀት መዋቅር በማዘመን የሕዝብ ተጠቃሚነትን በይበልጥ ለማረጋገጥ ትኩረት ተደርጓል- አፈ ጉባዔ አሕመድ ሽዴ - ኢዜአ አማርኛ
የምክር ቤቱን የአሠራርና የአደረጃጀት መዋቅር በማዘመን የሕዝብ ተጠቃሚነትን በይበልጥ ለማረጋገጥ ትኩረት ተደርጓል- አፈ ጉባዔ አሕመድ ሽዴ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 5/2019 (ኢዜአ)፦ የምክር ቤቱን የአሠራርና የአደረጃጀት መዋቅር በማዘመን የሕዝብ ተጠቃሚነትን በይበልጥ ለማረጋገጥ ትኩረት መደረጉን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አሕመድ ሽዴ ገለጹ፡፡
7ኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 1ኛ ዓመት የስራ ዘመኑ 3ኛ መደበኛ ስብሰባ ተካሂዷል።
ምክር ቤቱ ባካሔደው መደበኛ ስብሰባ የምክር ቤት ጉዳዮች አማካሪ ኮሚቴ አባላትን ለመሰየም የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ መርምሮ አጽድቋል።
በምክር ቤቱ የአሰራርና የአባላት የምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች አደረጃጀት፣ ተግባርና ኃላፊነት ለመወሰን የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብንም እንዲሁ።
በተጨማሪም የቋሚ ኮሚቴዎች ዕጩ አመራር እና አባላትን ምደባ አስመልክቶ የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ መርምሮ አጽድቋል።
አስራ ሶስት አባላት ያሉት የምክር ቤት ጉዳዮች አማካሪ ኮሚቴ አባላት እና ለ13 ቋሚ ኮሚቴዎች የሚያገለግሉ 26 ዋና እና ምክትል ሰብሳቢዎችን ሰይሟል፡፡
ከምክር ቤት አባላት የውሳኔ ሃሳቡን በተመለከተ ጥያቄ እና የተለያዩ አስተያየቶች ተሰንዝረዋል፡፡
የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እጸገነት መንግስቱ፤ ፍርድ ቤቶች የበጀት እና የሀብት ተጠቃሚ ተቋማት እንደ መሆናቸው መጠን፣ የክትትልና የቁጥጥር ሥርዓቱ አካል መሆን እንደሚገባቸው ገልጸዋል።
የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፈትህ ማሕዲ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ተቋማት ከሥራ ባህሪያቸው ጋር በሚስማማ መልኩ መደራጀት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ፈቃዱ ተሰማ በበኩላቸው፤ ምክር ቤቱ የተጣለበትን ሀገራዊ ሥራ በአግባቡና በብቃት ማከናወን እንዲችል የአማካሪና የቋሚ ኮሚቴዎችን አደረጃጀት አስቀድሞ ማዋቀር ግዴታ እንደነበር አስገንዝበዋል።
ከአባላት የቀረቡት አስተያየቶችና ግብአቶች በጣም ገንቢ በመሆናቸው ሙሉ በሙሉ ተወስደው የሚተገበሩ ይሆናሉ ብለዋል፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አሕመድ ሽዴ ለተነሱ አስተያየቶች ማብራሪያ ሲሰጡ፤ የምክር ቤቱን የአሠራርና የአደረጃጀት መዋቅር በማዘመን የሕዝብ ተጠቃሚነትን በይበልጥ ለማረጋገጥ ትኩረት ተደርጓል ብለዋል፡፡
ይህ አደረጃጀት የምክር ቤቱን የቁጥጥርና የክትትል አቅም ከማሳደጉም በላይ የሕዝብ ድምፅና ፍላጎት በፖሊሲና በሕግ አውጪነት ሂደት ውስጥ በአግባቡ እንዲንጸባረቅ የሚያስችል መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
በምክር ቤት አባላት የተሰጡ አስተያየቶች እንደ ግብዓት ተወስደው በቀጣይ በውሳኔ ሃሳቡ ተካተው ተግባራዊ እንደሚደረጉ አመላክተዋል፡፡