በምዕራብ ጎንደር ዞን የህብረተሰቡን ደህንነት ለማስጠበቅ የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
በምዕራብ ጎንደር ዞን የህብረተሰቡን ደህንነት ለማስጠበቅ የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ ናቸው
ገንዳውኃ፤ ጥቅምት 5/2019(ኢዜአ)፡- በምዕራብ ጎንደር ዞን ከፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የህብረተሰቡን ደህንነት ለማስጠበቅ የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ መሆናቸውን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ።
በዞኑ የተከናወኑ ሰላምን የማረጋገጥ ስራዎችንና የወደፊት አቅጣጫዎችን አስመልክቶ የዞኑ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና የጸጥታ መዋቅር አመራሮች የጋራ ውይይት አካሂደዋል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሆናለም አሻግሬ እንደገለጹት፤ በዞኑ ሰላምን ከማፅናት ጎን ለጎን የህዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ስራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል።
ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት በመሆኑም ህብረተሰቡ ከጸጥታ ሃይሎች ጋር በመሆን ሰላሙን በንቃት እንዲጠብቅ በማድረግ በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ለውጥ መመዝገቡንም ገልጸዋል።
በሀገር መከላከያ ሰራዊት ምዕራብ ዕዝ የ50ኛ ክፍለ ጦር አዛዥ ሌተናል ኮሎኔል ዘመኑ አለባቸው በበኩላቸው፤ ሰራዊቱ ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር የህብረተሰቡን ሰላምና ደህንነት እያስጠበቀ ይገኛል ብለዋል ።
ሰራዊቱ የህዝብን ሰላም ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን በመደምሰስ ህግና ስርዓትን የማስከበር ኃላፊነቱን በብቃት እየተወጣ እንደሚገኝም አስገንዝበዋል።
የዞኑ ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ደረሰ አዱኛ በበኩላቸው፤ ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር የተሰሩ ስራዎች ተጨባጭ ውጤት እያመጡ እንደሚገኙም ጠቅሰዋል።
ህብረተሰቡ የሰላሙ ባለቤት በመሆን አሁንም ጥርጣሬ የሚፈጥሩ አካላትን ለጸጥታ ሃይሎች በመጠቆም እያደረገ ያለውን ትብበር አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አስረድተዋል።
ባለፉት ሶስት ወራት 115 የሚሆኑ በጫካ የነበሩ ዜጎች የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው እጅ መስጠታቸውን አብራርተዋል።
የቋራ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አንዳርጋቸው አስማረ በበኩላቸው፤ በወረዳው ሰላምን ማረጋገጥ ለቀጣናው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ መሰረት መሆኑን በመገንዘብ በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።
አስተዳደሩ ከማህበረሰቡና ከጸጥታ ሃይሎች ጋር በመቀናጀት ህገ-ወጥ እንቅስቃሴዎችንና ስጋቶችን በመከላከል ዘላቂ ሰላም ለማስፈን እየሰራ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።
በመድረኩ የፌደራልና የክልል የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም የዞንና የወረዳ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።