ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የሪፎርም አጀንዳዎች እና ዓለም አቀፍ አጋርነቶች መሰረታቸው መደመር ነው- የብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 5/2019 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የሪፎርም አጀንዳ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነቶች በመደመር መርህ ላይ የተመሰረቱና የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም ማዕከል ያደረጉ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ(ዶ/ር) ገለጹ።

የ2026 የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት (IMF) እና የዓለም ባንክ ዓመታዊ ስብሰባ በታይላንድ ባንኮክ እየተካሄደ ይገኛል።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) የተመራ ልዑካን ቡድን እየተሳተፈ ይገኛል።

ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ከፐልስ ኦፍ አፍሪካ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት፣ መደመር ከኢትዮጵያዊያን እሴቶችና ታሪካዊ መሰረት የተቀዳ እና ለሀገሪቱ የልማት ጉዞ ተግባራዊና ምክንያታዊ አቅጣጫን የሚያመላክት እሳቤ ነው።

መደመር ከኢትዮጵያውያን እሴቶች የተቀዳ በመሆኑ፣ መነሻውም መድረሻውም ኢትዮጵያዊነት ነው። ለልማት ከምናደርገው ጥረት ውጭ ስለ ኢትዮጵያ ሌላ ርዕዮተ ዓለም የለንም ብለዋል።

የባንኩ ገዥ፤ የተተገበሩት ማሻሻያዎች ዓላማ ያለፉ ስህተቶችን ማረም፣ በነበሩ ስኬቶች ላይ መገንባት፣ የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ማጠናከር እና ለዘላቂ ብልፅግና ጠንካራ መሰረት መጣል መሆኑን አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር የምታደርገውን ግንኙነት በመደመር መርህ እንደምትመራ ጠቅሰው አጋርነቶች የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅሞች፣ ታሪካዊ ታላቅነት፣ ሥልጣኔ እና የኢኮኖሚ አቅም ማዕከል ያደረጉ መሆን እንዳለባቸው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ፍላጎቷን፣ አሁን ያለችበትን እና ወዴት መሄድ እንደምትፈልግ ጠንቅቃ ታውቃለች፤ በመሆኑም ከታሪካዊ፣ ሥልጣኔ እና ኢኮኖሚያዊ ከፍታዋ ጋር የሚመጥን የዲፕሎማሲ ግንኙነት ትሻለች ብለዋል።

ኢትዮጵያ በልማት ግቦቿ ላይ ትኩረት በማድረግ፣ በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ዘላቂ አጋርነት ለመገንባት እየሰራች መሆኑንም አመልክተዋል።

ሪፎርሙ ኢትዮጵያ የብዝሃ ኢኮኖሚ አማራጭን እንድትከተልና ከውስጥም ሆነ ከውጭ ከሚመጡ ድንገተኛ አደጋዎች የመቋቋም አቅሟን እንድታጠናክር ማስቻሉ ነው ያብራሩት።

ኢትዮጵያ በፈተናዎች ውስጥ ሆና የ10.2 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገቧን፣ የኤክስፖርት ገቢም በአራት እጥፍ አድጎ 11.2 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር መድረሱን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም በውጭ ምንዛሬ ክምችት ላይ መሻሻል መታየቱን ገልጸዋል።

እነዚህ ለውጦች ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ አቋሟን ለማጠናከር እና አስተማማኝ ዓለም አቀፍ አጋር ለመሆን ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳዩ ናቸው ብለዋል።

በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት እና የዓለም ባንክ ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያ በውጭ ዕዳ ሽግሽግ ላይ ያገኘችውን ውጤት እያቀረበች ሲሆን፣ በልማት ፋይናንስ እና ኢንቨስትመንት ዘርፍም ትብብሯን ለማስፋት እየሰራች መሆኑን ገልጻለች።

ከሁለትዮሽ አበዳሪዎች ጋር የተደረገው ስምምነት መጠናቀቁንና እንደ ዩሮቦንድ ካሉ ውጭ የንግድ አበዳሪዎች ጋር ያሉ ጉዳዮችም የመጨረሻ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የባንክ ዘርፉን ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት ማድረጓ፣ የባንኮችን ውድድር ለማጠናከር፣ ከፍተኛ ካፒታል ለመሳብ እና አዳዲስ የፋይናንስ አሰራሮችን ማስተዋወቅን አላማ ያደረጉ መሆናቸውን አመልክተዋል።

የሀገር ውስጥ ባንኮች ለዓለም አቀፍ ውድድር ብቁ እንዲሆኑ፣ የፋይናንስና የአሰራር አቅማቸውን እንዲገነቡ ብሔራዊ ባንክ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም