የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት ለአካባቢው የቱሪዝም ዕድገትን እያመጣ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት ለአካባቢው የቱሪዝም ዕድገትን እያመጣ ነው
ጎንደር፤ ጥቅምት 5/2019 (ኢዜአ) ፡-የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት ለአካባቢው የቱሪዝም ዕድገትን እያመጣ መሆኑን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን አስተዳዳሪ አቶ አወቀ አስፈሬ ገለፁ።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን "ዲጂታል አጀንዳ እና ሰው ሠራሽ አስተውሎት አዲስ ቅኝት" በሚል መሪ ሐሳብ የሚከበረውን የቱሪዝም ቀን በውይይት መድረክ በጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት አክብሯል።
ዋና አስተዳዳሪው በወቅቱ እንደገለጹት፤ የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት ለአካባቢው የቱሪዝም ዕድገት ትንሣኤን ያመጣ ነው።
ዞኑም ጎርጎራን ከጎንደር ጋር በማስተሳሰር የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ ባደረገው ጥረት በአካባቢው የነበረውን የጸጥታ ሥጋት ማስወገድ መቻሉን ገልጸዋል።
ይህም የውጭ አገራትና የአገር ውስጥ ጎብኚዎች ወደ አካባቢው በመምጣት የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ቅርሶችን በመጎብኘት እንዲዝናኑ ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር ማስቻሉን አመልክተዋል።
በዞኑ ያለውን እምቅ የቱሪስት መዳረሻ አልምቶ ለሕዝብ ጥቅም ለማዋል እየተሠራ መሆኑን ጠቁመው፤ የመሠረተ ልማት ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ለመቅረፍ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
የተያዘው ዓመትም የተጀመሩ ሥራዎችን በማጠናከርና አዳዲስ የልማት ፕሮጀክቶችን በማስጀመር የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሠራም ገልጸዋል።
የዞኑ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ድግስ መለሰ በበኩላቸው፤ ዞኑ በርካታ ጥንታዊ ገዳማት፣ አብያተ መንግሥታትና የተፈጥሮ ጸጋዎች መገኛ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም ጎብኚዎች ወደ አካባቢው ሲመጡ እንደ ጎርጎራ ሪዞርት ያለ የተሟላ ምቹ ማረፊያ፣ የተረጋጋ ሰላም እና የሰለጠነ መስተንግዶ ለማቅረብ እየተሠራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
የከተማውን ታሪካዊ መስተጋብር ታሳቢ በማድረግ የአካባቢውን የቱሪዝም ዕድገት በዲጂታል ሚዲያ በማስተዋወቅ ተጨማሪ ቱሪስቶችን ለመሳብ እየተሠራ ነው ብለዋል።
በዞኑ ያሉ ነባር ቅርሶች ይዘታቸውን ሳይለቁ የጥገና ሥራዎች በየጊዜው እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመው፤ በተያዘው ዓመት ብቻ የዘጠኝ ቅርሶች ጥገና እየተካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል።
በውይይት መድረኩ የተሳተፉ የዞኑ ሥራ ኃላፊዎች፣ ባለሙያዎችና የአካባቢው ነዋሪዎች የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርትን ጨምሮ በዙሪያው ያሉ ታሪካዊ መዳረሻዎችን ጎብኝተዋል።