ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ጠንካራ የኢኮኖሚ ሥርዓት የመገንባት ጉዞዋን አጠናክራ ትቀጥላለች

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 5/2019 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ተወዳዳሪ እና ጠንካራ የኢኮኖሚ ሥርዓት ለመገንባት የያዘችውን ጉዞ አጠናክራ እንደምትቀጥል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ገለጹ።

የ2026 የዓለም ገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) እና የዓለም ባንክ ዓመታዊ ስብስባ በታይላንድ ባንኮክ እየተካሄደ ነው።


 

ከዓመታዊ ስብሰባው ጎን ለጎን "Finance For Development Lab" የተሰኘ ተቋም " ህይወት ከእዳ በኋላ፤ ሀገራት በድህረ ቀውስ ወቅት እንዴት ማገገም እና ማደግ ይችላሉ?" በሚል ርዕስ ያዘጋጀው ውይይት ተካሄዷል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በውይይቱ ላይ የተሳተፉ ሲሆን የባንኩ ገዥ የኢትዮጵያን ተሞክሮ አንስተዋል።

የአንድን ሀገር የዕዳ ችግር መፍታት ለዘላቂ እድገት የመጀመሪያው እርምጃ እንጂ የመጨረሻው ግብ አለመሆኑን ገልጸዋል።

ሀገራት በፍጥነት አዲስ ኢንቨስትመንት ለመሳብና ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት ለማምጣት ወቅቱን የጠበቀ የዕዳ ክፍያ ማቃለያ ወይም እፎይታ ማግኘት፣ የተቀናጀ የአበዳሪዎች ትብብር እንዲሁም አስተማማኝ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሞችን በአስቸኳይ መተግበር እንዳለባቸው አንስተዋል።

በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ከዕዳ ተላቀው የራሳቸውን የልማት አጀንዳዎች በራሳቸው ማከናወን እንዲችሉ፣ የዓለም አቀፉ የፋይናንስ ሥርዓት ለሀገራቱ ችግር ፈጣንና ተገቢ ምላሽ መስጠት በሚያስችል መልኩ ማሻሻያ ሊደረግበት እንደሚገባ አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ ይበልጥ ጠንካራ፣ በገበያ ውስጥ ተወዳዳሪና በኢንቨስትመንት የሚመራ የኢኮኖሚ ሥርዓት ለመገንባት የጀመረችውን ጉዞ አጠናክራ እንደምትቀጥልም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም