ቀጥታ፡

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ጊዜና ወጪ እንድንቆጥብ አስችሎናል

ሸገር ፤ጥቅምት 5/2019 (ኢዜአ)፦ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የጊዜ ብክነትን ከማስቀረቱ ባሻገር፣ ላልተፈለገ ወጪ እንዳይጋለጡ እንደረዳቸው በሸገር ከተማ የቡራዩ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ

የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥን ማዘመን፣ መልካም አስተዳደርን ማስፈን እና የቢሮክራሲ ማነቆዎችን ማስወገድ የመንግስት ዋና ትኩረት ከሆኑ ጉዳዮች መካከል ይጠቀሳሉ።


 

ቀደም ሲል ተገልጋዮች ለአንድ ጉዳይ ማስፈጸሚያ በተለያዩ ቢሮዎች እና ተቋማት መካከል የመመላለስ፣ ረጅም ጊዜ የመጠበቅ፣ እንዲሁም ለአላስፈላጊ ተጨማሪ ወጪዎች የመጋለጥ ሰፊ እንግልት ይደርስባቸው ነበር።

ይህ አሰራር አላስፈላጊ የጊዜና የወጪ ብክነትን ከመፍጠሩ ባሻገር፣ ለሙስና እና ለብልሹ አሰራር ቀዳዳዎችን በመክፈት የተገልጋዩን ህዝብ እርካታ ዝቅ በማድረግ የመንግስትና የህዝብ ግንኙነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሲፈጥር ቆይቷል።

ይህን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የተዘረጋው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የተበታተኑ አሰራሮችን በአንድ ጣሪያ ስር በማቀናጀትና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ወረቀት-አልባ አሰራርን በመተግበር ላይ ይገኛል።

አዲሱ አሰራር የባለጉዳዮችን እንግልት በመቀነስ፣ የአገልግሎት አሰጣጡን ግልጽነትና ፍጥነት በማሳደግ እንዲሁም የዜጎችን እርካታ በማረጋገጥ ረገድ ከፍተኛ ለውጥ እያስመዘገበ ይገኛል።


 

በሸገር ከተማ ቡራዩ ክፍለ ከተማ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች መካከል አቶ ተመስገን ባለጠ እንደተናገሩት፣ ቀደም ሲል አንድ ጉዳይ ለማስፈጸም መመላለስና ረጅም ጊዜ የሚጠይቅ እንደነበር ገልጸው፣ በአሁኑ ወቅት ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ ቀልጣፋ አገልግሎት በማግኘት ላይ እንገኛለን ብለዋል።

ይህ የተጀመረው አገልግሎት ከፍተኛ የማህበረሰብ ተጠቃሚነትን ያረጋገጠ እና በመንግስትና በማህበረሰቡ መካከል እምነትን ለመፍጠር ከፍተኛ ሚና ያለው መሆኑን ጠቁመዋል።


 

ወጣት ባጫ በቃናም፤ አገልግሎቱ በአንድ ቦታ መገኘቱ መመላለስና የጊዜ መዘግየትን በማስቀረት፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ በቂ አገልግሎት ለማግኘት እንዳስቻላቸው ገልጿል።

ወይዘሮ አበራሽ መኩሪያ በበኩላቸው፣ ቀደም ሲል አንድ ጉዳይ ለማጠናቀቅ መመላለስና ረጅም ጊዜ ይወስድ እንደነበር አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅት በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በአጭር ጊዜ ውስጥ ፈጣንና ጥራት ያለው አገልግሎት በማግኘት ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።


 

የቡራዩ ክፍለ ከተማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ኢሳያስ መኮንን በበኩላቸው እንደገለጹት፣ አገልግሎቱ የባለጉዳዮችን መመላለስ በማስቀረት ተገልጋዮች ከአንድ መስሪያ ቤት ወደ ሌላ መስሪያ ቤት የሚመላለሱበትን አሰራር የፈታ ነው።

ይህም ማህበረሰቡ ለሙስና እንዳይጋለጥ በማድረግ በመንግስትና በህዝብ መካከል ግልጽነትን ያጎለበተ መሆኑን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ቀደም ሲል በተለያዩ መስሪያ ቤቶች ተበታትኖ የነበረውን አገልግሎት በአሁኑ ወቅት በአንድ ቦታ ማሰባሰብ መቻሉ ለማህበረሰቡ ትልቅ ጥቅም የፈጠረ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም