ቀጥታ፡

አዲስ ከተመሰረተው መንግሥት ጎን በመቆም ሰላም ለማጽናትና ልማትን ለማፋጠን እንሰራለን

ገንዳውኃ፤ጥቅምት 5/2019 (ኢዜአ)፦ አዲስ የተመሰረተው መንግስት ሰላምን ለማጽናት እና ልማትን ለማፋጠን የሚያደርጋቸውን ጥረቶች እንደሚደግፉ የገንዳውኃ ከተማ ነዋሪዎች  ገለጹ።

ነዋሪዎቹ ለዘላቂ ሰላም ግንባታ እና ሁለገብ ዕድገት መረጋገጥ ከመንግሥት ጎን በመሰለፍ በትኩረት ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

የከተማዋ ነዋሪ የሆኑት አቶ ሰጠኝ ካሴ ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቀጣይ አምስት ዓመታት የሚከናወኑ የልማትና የሰላም ጉዳዮች ላይ ያስቀመጡት አቅጣጫ ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ተገንዝበናል ብለዋል።


 

የተቀመጠው አቅጣጫ ስኬታማ እንዲሆንና ህብረተሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን መንግሥት በሚያደርገው ጥረት ውስጥ የድርሻቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ነው የሚገልጹት።

በተለይ ሰላምን መጠበቅና ማጽናት የሁሉም ዜጋ ግዴታ በመሆኑ አዲሱ መንግሥት ያቀዳቸውን ግቦች እንዲሳኩ በማድረግ የአገራችንን ዕድገት ለማፋጠን እንሠራለን ነው ያሉት።

ሌላው የከተማዋ ነዋሪ ሹመት ምስጋናው በበኩላቸው፤ የንግድ እንቅስቃሴዎችንና የኅብረተሰቡን ማህበራዊ ሕይወት የተሳለጠ ለማድረግ ሰላምን ማጽናት አስፈላጊ በመሆኑ ለዚሁ ስኬታማነት የበኩላችንን እንወጣለን ብለዋል።

ወጣቱ የነገ ሀገር ተረካቢ በመሆኑ ከመንግሥት ጋር ተቀናጅቶ በመሥራት መጪውን ጊዜ ብሩህ ማድረግ አለበት ያለው ደግሞ ሌላው የከተማዋ ነዋሪ ወጣት አሰፋ ዘሪሁን ነው።


 

መንግሥት በአሁኑ ወቅት ሥራ አጥነትን ለመቀነስ  በሚያደርገው ጥረት ወጣቶች ተሳትፎአችንን ማሳደግ ይገባናል ነው ያለው።

የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶችም ዳር እንዲደርሱ የሚጠበቅበትን ድጋፍ እንደሚያደርግም ነው የተናገረው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም