ቀጥታ፡

የባህር በር ጥያቄያችን ከግብ እንዲደርስ የበኩላችንን እንወጣለን 

አዳማ ፤ጥቅምት 5/2019 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በሴራ የተወሰደባትን የባህር በር ለማስመለስ የበኩላቸውን እንደሚወጡ የአዳማ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ።

ኢትዮጵያ በታሪኳ ለዘመናት የቀይ ባህር በር ባለቤት በመሆን አለም አቀፍ ንግድን፣ የባህር ሃይልን እና የጂኦፖለቲካ ተደማጭነትን ስትጠቀም የቆየች ጥንታዊት የባህር ሀገር ናት። 

ሆኖም ግን ታሪካዊ ጠላቶቿ በሸረቡት ሴራ  ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ ከ120 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያላት ብቸኛዋ የባህር በር አልባ የዓለም ሀገር ሆናለች። 

ይህም ለውጭ ንግዷ የመሸጋገሪያ እና የሎጅስቲክስ ወጪ እንድታወጣ፣ እንዲሁም ለኢኮኖሚና ለብሔራዊ ደህንነት ተጋላጭነቷ እንዲጨምር አድርጓታል።

በአሁኑ ወቅት ግን ኢትዮጵያ የባህር በር ተደራሽነትን መልሳ ለማግኘት እያደረገች ያለችው እንቅስቃሴ የሀገሪቱን ወቅታዊ የጂኦፖለቲካ እና የቀጣናው ፖለቲካ ሁኔታ የሚያንጸባርቅ ነው።

በጉዳዩ ላይ ለኢዜአ አስተያየት የሰጡት የአዳማ ከተማ ነዋሪዎች እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በታሪካዊ ስህተት ያጣችውን የባህር በር መብት ለማስከበር  የተጀመረውን ዲፕሎማሲያዊ እና ስትራቴጂካዊ ጥረት ሙሉ በሙሉ ይደግፋሉ። 

ይህንን ብሔራዊ ህልም ከግብ ለማድረስ እና የሀገሪቱን የባህር በር ተደራሽነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ማንኛውም እንቅስቃሴ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት ዝግጁ መሆናቸውንም ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።

ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ድሪባ ጫላ እንደገለፁት ቀይ ባህር የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብት ነው።

የእኛ ዋና አላማ በሴራ የተነጠቅነውን የባህር በር ማስመለስ ነው ያሉት አቶ ድሪባ፣ እውነታው የቀይ ባህር ተደራሽነት ለትክክለኛ ባለቤቱ ለኢትዮጵያ እንዲመለስ ማድረግ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ  አቶ ጥላሁን ራጎ በበኩላቸው፤ የቀድሞ ብሔራዊ መከላከያ ሠራዊት አባል በመሆን በአሰብና ምፅዋ በመኖር የሀገር ዳር ድንበር ሲያስጠብቁ እንደነበር አስታውሰዋል።

የባህር በር ጥያቄ ከግብ እንዲደርስ ከመንግሥት ጎን ሆነን አስፈላጊውን ድጋፍ እናደርጋለን ብለዋል።

ያጣነው የባህር በር የሚያስቆጭ ነው ያሉት አቶ ጥላሁን፤ ትውልዱ በሴራ ያጣውን ሀብት ለማስመለስ በቁጭት መነሳቱንም ገልጸዋል።

የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄው፤ ተስፋችን እንዲለመልም ያስቻለ ነው ያሉት ደግሞ ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ አቶ መለሰ አያሌው ናቸው።

ኢትዮጵያ በውስጥና በውጭ ታሪካዊ ጠላቶች ሴራ የተነጠቀችውን የባህር በር መልሳ እንድታገኝ የተጀመረው እንቅስቃሴና እርምጃ እንዲሳካ የሚጠበቅብንን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነን በማለት አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም