የደረጃዎች አጠቃቀም የምርትና የአገልግሎት ጥራትን በማሻሻል ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና አለው - ኢዜአ አማርኛ
የደረጃዎች አጠቃቀም የምርትና የአገልግሎት ጥራትን በማሻሻል ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና አለው
አዲስ አበባ፤ጥቅምት 5/2019 (ኢዜአ)፦የደረጃዎች አጠቃቀም የምርትና የአገልግሎት ጥራትን ከማሻሻል ባለፈ ንጹሕና ተመጣጣኝ ዋጋ ያለው ኃይል ለማስፋፋት እንዲሁም ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና እንዳለው የኢትዮጵያ የደረጃዎች ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር መሰረት በቀለ (ዶ/ር) ገለጹ።
የኢትዮጵያ የደረጃዎች ኢንስቲትዩት በየዓመቱ የሚከበረውን የዓለም የደረጃዎች ቀን ዘንድሮ “ተመጣጣኝ ዋጋ ያለውና ንጹሕ ኃይል” በሚል መሪ ሐሳብ እያከበረ ይገኛል።
ቀኑን ምክንያት በማድረግም በጥራትና በደረጃዎች ላይ ባተኮሩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ከአምራቾችና ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ በማካሄድ ላይ ነው።
በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት ዋና ዳይሬክተሯ መሰረት በቀለ (ዶ/ር) እንደገለፁት፤ ደረጃዎች ንጹሕና ተመጣጣኝ ዋጋ ያለውን ኃይል ለማስፋፋት፣ የሀብት አጠቃቀምን ለማሻሻልና የኃይል አቅርቦትን በተቀናጀና በጥራት በተመሠረተ መንገድ ለማስተዳደር ቁልፍ ድርሻ አላቸው።
ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ሀብት በመጠቀም በኃይል ማመንጨት ዘርፍ ተጽዕኖ ፈጣሪ ለመሆን እያደረገች ያለችውን ጥረት ያነሱት ዋና ዳይሬክተሯ፤ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ በታዳሽ ኃይል ልማት የተከናወኑ አበይት ሥራዎች ለዚህ ማሳያ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የኃይል ፍላጎት ከቴክኖሎጂያዊ፣ ከኢኮኖሚያዊና ከማኅበራዊ እድገት ጋር ተያይዞ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል።
ይህንን ፍላጎት ለማሟላት የሚደረጉ ጥረቶች ከደረጃዎች ጋር በተቀናጀ መንገድ መመራታቸው የኃይል አቅርቦትንና ቅልጥፍናን ከማሻሻሉም በላይ የሀብት ቁጠባን እንደሚያግዝ አብራርተዋል።
በተጨማሪም ደረጃዎች የማኅበረሰቡን ገንዘብና ጉልበት በመቆጠብ፣ የምርትና የአገልግሎት ጥራትን በማረጋገጥ እንዲሁም የሸማቾችን ተጠቃሚነት በማሳደግ ረገድ የላቀ ፋይዳ እንዳላቸው አስረድተዋል።
በዚህ ረገድ የጥራት መሠረተ ልማት ተቋማት የሀገሪቱን የልማት ግቦች ለማሳካት የሚያስችሉ የጥራት ሥርዓቶችን በማስፋፋት፣ የምርትና የአገልግሎት ደረጃዎችን በማዘጋጀትና የቴክኒክ ድጋፍ በመስጠት በኩል የሚያከናውኑት ተግባር እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል።
ኢንስቲትዩቱ ከ60 ዓመታት በላይ በተለያዩ አደረጃጀቶችና ስያሜዎች ሲሠራ መቆየቱን አስታውሰው የተቋሙን ሕጋዊና ተቋማዊ አቅም ለማጠናከር፣ የራሱ የሆነ የደረጃዎች ሕግ እንዲኖረው ለማድረግ፣ አሠራሩን ለማዘመንና አገልግሎቶቹን ተደራሽና ቀልጣፋ ለማድረግ በርካታ የማሻሻያ ሥራዎች መከናወናቸውን አስረድተዋል።
የደረጃዎች ሥርዓት ውጤታማነት በተቋማት ወሰን ውስጥ ብቻ ሳይወሰን ለዜጎች ተጨባጭ ጥቅም ማስገኘት እንዳለበት ጠቁመው የሚከናወኑ ሥራዎች የማኅበረሰቡን ፍላጎት መመለስና የሀገሪቱን ዘላቂ ልማት ማገዝ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።