ቀጥታ፡

በግብርና ዘርፍ የሴት አርሶና አርብቶ አደሮችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ ነው

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 5/2019 (ኢዜአ)፦የመደመር መንግሥት በግብርና ዘርፍ የሴት አርሶና አርብቶ አደሮችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) ገለጹ።

ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ፤

የግብርና ሚኒስቴር ዓለም አቀፍ የሴት አርሶና አርብቶ አደሮች ቀንን ለመጀመሪያ ጊዜ በሀገር አቀፍ ደረጃ በአዲስ አበባ በተለያዩ መርሃ ግብር እያከበረ ይገኛል።


 

የሴት አርሶ አርብቶ አደሮችን የመሬት ባለቤትነት መብት፣ የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽነትና የግብርና ቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ለማሳደግ በተከናወኑ ተግባራት ውጤቶች ተመዝግበዋል።

ዓለም አቀፍ የሴት አርሶና አርብቶ አደሮች ቀን በሀገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ መርሃ ግብሮች መከበሩም የሴቶችን የግብርና ዘርፍ ማህበራዊና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት የማላቅ ጥረት የሚያጎላ ይሆናል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ ሴቶች በግብርና ምርታማነትና የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ሂደት ውጤታማና ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ ተግዳሮቶች ነበሩ።


 

ለአብነትም የመሬት ባለቤትነት መብት አለመረጋገጥ፣ የፋይናንስ አገልግሎቶች ውስንነትና የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነትን የሚቀንሱ ቴክኖሎጂዎችን አቅርቦት ውስንነት ይገኙበታል ብለዋል።

የመደመር መንግሥት ባለፉት ዓመታት የሴት አርሶና አርብቶ አደሮችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያሻሽሉ አካታችና አሳታፊ የግብርና አሰራር ስርዓቶች መዘርጋቱን ገልጸዋል።

በዚህም የሴት አርሶና አርብቶ አደሮችን የመሬት ይዞታ መብት በማረጋገጥ የፋይናንስ አቅርቦትን በማሳደግና የግብርና ማስፋፊያ አገልግሎቶችን ተደራሽ ማድረግ እየተቻለ መሆኑን ተናግረዋል።

እነዚህ እርምጃዎችም ሴቶች በግብርናው ዘርፍ ከአነስተኛ እስከ ትላልቅ የእርሻ ይዞታና የግብርና ኢንቨስትመንት ድረስ የሚሰማሩበትን ዕድል በመፍጠር ምርታማነትን እያሻሻለ መሆኑን አስረድተዋል።


 

ይህም የሴቶችን የምርታማነት አቅም በማሳደግ በገበያ ተሳትፎ፣ በገቢ ማስገኛና በግብርና ኢንቨስትመንት የሚኖራቸውን ሚና ለማጠናከር የሚያግዝ መሰረት መፍጠሩን አመላክተዋል።

በቀጣይም የሴት አርሶና አርብቶ አደሮችን የግብርና ዘርፍ የምርታማነት ተወዳዳሪነትና ውጤታማነት በማላቅ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማሻሻል እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

ባለድርሻ አካላትም ሴት አርሶና አርብቶ አደሮች ያሉባቸውን ተግዳሮቶች ለመፍታትና በግብርናው ዘርፍ ያላቸውን አቅም ለማሳደግ የሚያግዝ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

ይህም የሴት አርሶና አርብቶ አደሮችን የመሬት፣ የፋይናንስና የቴክኖሎጂ ተደራሽነት በማሻሻል በግብርና ዘርፍ ያላቸውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም